
ለሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የአስጎብኝ ማህበር አባላትና ለሌሎች አገልግሎት ሰጪ አካላት ስልጠና መስጠት ተጀመረ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካን ወርልድ ላይፍ ፋውንዴሽን ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የአስጎብኝ ማህበር አባላትና ለሌሎች አገልግሎት ሰጪ አካላት ፓርኩን ከመጠበቅ፣ ከማስተዋወቅ፣ ከማስጎብኘትና ለሀገርና ለአካባቢው የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን ከመስራት አኳያ በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና ከዛሬ ሚያዚያ 30/2015 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ 14 ቀናት በኤች ዲ ፒ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መሰጠት ጀመረ፡፡
በዚህ የስልጠና መርሃ ግብር የዩኒቨርሲቲያችን የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጨቅሉ፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታው፣ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አዛናው ከፍያለው፣ ከአፍሪካን ወርልድ ላይፍ ፋውንዴሽን ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ጥበቡ የለምፍርሃት፣ የአስጎብኝ ማህበራት አመራሮችና አስጎብኝዎች እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ከሀገርም አልፎ የዓለም ሀብት በመሆኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከተከሰተበት ችግር ለማውጣት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት እንደሆነ በመርሃ ግብሩ በመክፈቻ ንግግራቸው የሚያወሱት የዩኒቨርሲቲያችን የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጨቅሉ፣ ፓርኩን ከመጠበቅና ከማስተዋወቅ አንፃር በጋራ ስራዎችን በመለየት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ቢኒያም አያይዘውም የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችንና መተግበሪያዎችን በመጠቀም የፓርኩን ኢሜጅ ወይም ምስል መገንባት፣ ፓርኩን ከመጠበቅና ከማስጎብኘት አንፃርም ከመቼውም በበለጠ መሰራት እንደሚገባና በዩኒቨርሲቲው፣ በክልል፣ በፌዴራልና በፓርኩ ፅ/ቤት በኩል ፓርኩን ከማስተዋወቅ አንፃር ስትራቴጅክ በሆነ መልኩ ምን መሰራት እንዳለበት ለይቶ መስራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ በስፋት አብራርተዋል፡፡ ወደፊትም በአማራ ክልል ቱሪስቶች የሚቆዩባቸውን ጊዚያት ረዘም ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው የበለፀገው መተግበሪያ ወደ ተግባር እንዲገባ እንደሚደረግ ዶ/ር ቢኒያም አክለው ያነሱ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲው በኩል አስፈላጊውን ሁሉ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነትም ገልፀዋል፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዛናው ከፍያለው በበኩላቸው ፓርኩ ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች አንዱ የሆነውና ከጎንደርዩኒቨርሲቲው ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስረው የትምህርትና የምርምር ማዕከል ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ያወሱ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በተለይም ፓርኩ ቃጠሎ በደረሰበት ጊዜ ያደረገው ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ፣ በተለያየ ጊዜ ለማኔጅመንት ክፍሉና ለሌሎች አአገልግሎት ሰጪ አካላት በተደጋጋሚ ስልጠናዎችን በመስጠት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ አሁን ላይ ፓርኩ በትልቅ ችግር ውስጥ እንደሚገኝና ያለንው የህግ መላላት፣ ማህበረሰቡ በከፋ ድህነት ውስጥ መኖሩን፣ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚለዩ ችግሮችን በሚሰሩ የምርምር ስራዎችና በሌሎች ድጋፎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ግምት ውስጥ በማስገባት ድጋፉ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ አቶ አዛናው አያይዘው ገልፀዋል፡፡ የሚሰጠው ሰልጠናም የአገልግሎት ሰጪዎችን የእውቀት ክፍተት የሚሞላና ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚመጡ ጎብኝዎች በሚያገኙት አገልግሎት የበለጠ እንዲረኩና ስለሀገራችንም የተሻለ እውቅና እንዲኖራቸው ከማድረግ አንፃር ስልጠናው በጣም ወሳኝ እንደሆነ አቶአዛናው ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካን ወርልድ ላይፍ ፋውንዴሽን በፈረንጆቹ ከ2014 ጀምሮ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ መስራት እንደጀመረ የፕሮግራሙ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ጥበቡ የለምፍርሃት አውስተው፣ ፕሮግራሙ የፓርኩን ማኔጅመንት አቅም ማጠናከር፣ የማኔጅመንት መሰረተ ልማቶችን ማሳደግ፣ ለቱሪዝም የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ማሳደግና ማሻሻል፣ በፓርኩ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳትና እፅዋትን መጠበቅና ተፈጥሮን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንባቸውን ስራዎችን ባለፉት አምስት አመታት የትኩረት አቅጣጫዎች ሆነው ሲሰራባቸው መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ እነዚህን የትኩረት አቅጣጫዎች ከማስቀጠል በተጨማሪ የምርምር ስራዎችን ከተቋማት ጋር በማስተሳሰር በኩል በስፋት እንደሚሰራበትም ሰፊ ማብራሪያ ሰጠዋል፡፡
በመቀጠል በዩኒቨርሲቲው መምህራን ስልጠናው መሰጠት የጀመረ ሲሆን፣ በፓሩኩ ታሪክ፣ የመሬት አቀማመጥ፣ ያለው የእፅዋትና የእንስሳት ስርጭት፣ የዱር እንስሳት ቱሪዝም፣ የአዕዋፍ ጥናትና ሌሎች ተያያዥ ርዕሶች ላይ ያተኮረ ስልጠና በንድፈ ሃሳብና በተግባር እንደሚሰጥ በመርሃ ግብሩ ተገልጿል፡፡