
ለ2015 ዓ/ም በጀት ዓመት የ1ኛው ዙር ለመስክና ቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም ለሚወጡ ተመራቂ ተማሪዎች ቅድሚያ ስልጠናና ኦረንቴሽን ተሰጠ
ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ2015 ዓ/ም በጀት ዓመት የ1ኛው ዙር ለመስክና ቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም ለሚወጡ ተመራቂ ተማሪዎች ዛሬ ሚያዚያ 10/ 2015 ዓ/ም በሳይንስ አምባ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ቅድሚያ ስልጠናና ኦረንቴሽን ተሰጠ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመስክ የቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም፣ ተማሪዎቹ የቲቲፒ ቢሮ በሚያዘጋጃቸዉ የዳሰሳ ጥናት መጠይቆች መሰረት በየተመደቡበት አካባቢ የሚኖረውን የማህበረሰብ ችግር ለመፍታት በማረሚያ ቤቶች ፣ በትምህርት ቤቶች ፣በጤና ጣቢያዎች፣ በሀይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሰዎች በጋራ በሚኖሩባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በመገኘት ዳሰሳዊ ጥናቱን አካሂደው ችግሮቹን ይለያሉ፡፡ ችግሮቹ ከተለዩ በኋላ ደግሞ እነኝህን የማህበረሰብ የጤና ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመንደፍና ልዩ ልዩ አጋር አካላትን በማፈላለግ ፕሮጀክቶችን በመስራት የማህበረሰቡን ችግር ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲፈቱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከቲቲፒ ፕሮግራም ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለውና ተቋሙ ከተመሰረተበት ከ1954 ዓ/ም ጀምሮ የተቋቋመ ፕሮግራም እንደሆነ የኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ መርሃ ግብሩን አስመልክቶ ባቀረቡት ንግግር ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር አስማማው አያይዘውም ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ የተማሩትን ትምህርት በማህበረሰቡ ውስጥ ገብተው በተግባር የሚያገለግሉበት በመሆኑ ለዚህም ይበልጥ ተጠቃሚዎች እራሳቸው ተማሪዎች በመሆናቸው በሚኖራቸው የቆያታ ጊዜ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በዚህ በትምህርት ዘመኑ የመስክ የቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም ከ5ኛ አመት የህክምና ተማሪዎች በተጨማሪ የሰርጅካል ነርስ ፣ የኢመርጀንሲ ነርስ፣ የፔዲያትሪክ ነርስ፣ የአካባቢ ጤና አጠባበቅና የሙያ ደህንነት እንዲሁም የሥነ-አዕምሮ ተመራቂ ተማሪዎች ከሚያዚያ 14/2015 ዓ/ም ጀምሮ በደባርቅ፣ በቆላድባ፣ በወሮታና በጠዳ ከተሞች እንደሚወጡ የፕሮግራሙ አስተባባሪ መ/ር ጋረደው ታደገ ፕሮግራሙን አስመልክተው ባቀረቡት ጽሑፍ ገልፀዋል፡፡ የፕሮግራሙን ዓላማ፣ ተማሪዎች በሶስት ሳምንት ቆይታቸው የሚያከናውኗቸውን ዋና ዋና ተግባራት፣ የግምገማ ስልቶችንና ከተማሪዎች በሚጠበቁ ተግባራት ዙሪያም መ/ር ጋረደው አክለው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠል በዘርፉ ትልቅ ልምድ ያላቸውና አንጋፋው ተመራማሪ ፕ/ር አምሳሉ ፈለቀ የመስክ የቡድን ስልጠና (TTP) ፕሮግራም ታሪካዊ ዳራ፣ ስለ ፕሮግራሙ ፍልስፍናና አጠቃላይ ያላቸውን ልምድ አስመልክቶ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በሌሎች አሰልጣኝ መምህራን ደደግሞ በተመረጡ ርዕሶች ዙሪያ ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡