በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራን የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ርክክብ ተፈፀመ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ተመራማሪ መምህራን የኮሮና ቫይረስን /covid19/ ለመከላከል የሚረዱ እና የህክምና አገልግሎቱን የሚያግዙ የፈጠራ ስራዎች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይንን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነሐሴ 27/2012 ዓ/ም ከኢንስቲትዩቱ ቤተ ሙከራ ርክክብ ተደረጓል፡፡

በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን ፕሮግራሙን አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም የፈጠራ ባለቤቶችን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለህዝባቸውና ለወገናቸው ይረዳል ብለው በመስራት ለውጤት በመብቃታቸው ያላቸውን አድናቆት የገለፁ ሲሆን፣ ይህ ፈታኝ ወቅት የተለያዩ ፈጠራዎች የወጡበት፣ ህዝብ ለህዝብ፣ ወገን ለወገን መረዳዳት የታየበት መሆኑን አውስተዋል፡፡ ዶ/ር አሥራት አያይዘው የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት በርካታ የፈጠራ ስራዎችን እንደሠሩና እነዚህ የፈጠራ ስራዎች ለዛሬ ችግር መፍቻ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚገጥሙ ፈተናዎች ሁሉ ችግርን የመቋቋም አቅም እንዳለ የሚያሳይ መሆኑን በመግለፅ ለተመራማሪዎች ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል፡፡ የተገኙ የፈጠራ ሥራዎች ከቤተ ሙከራ ወጥተው የወጣቶች ሥራ ፈጠራ፣ ለሕዝብ አገልግሎት እና ለገቢ ማመንጫ መዋል እንዳለባቸው በአጽንኦት አሳስበዋል።

በመቀጠልም የፈጠራ ባለቤቶች የሆኑት መ/ር ጥበቡ አለነ፣ መ/ር ግዛቸው ደረጀ፣ መ/ር ታደለ መለሰ፣ መ/ር አሸናፊ ተስፋዬ እና ወጣት ጌታቸው ዓለምነህ በቡድን በመሆን የሰሯቸውን ከንክኪ ውጭ ሳኒታይዘርና የሳሙና መርጫ፣ የግሉኮስ ማንጠልጠያ፣ አውቶማቲክና ሜካኒካል የእጅ መታጠቢያ፣ የበር መክፈቻና መዝጊያ፣ ለጤና ባለሙያዎች የፊት ጭንብል፣ ሜካኒካል ቬንቲሌተር፣ ድሮውን፣ የመተንፈሻ ቫልቭ፣ ማስክ ማስረዘሚያ፣ ለ”ATM” እና ለ”keyboard” መገልገያ ቁስ ሰርተው በከፍተኛ አመራሩ ፊት አሰራሩንና አጠቃቀሙን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት ሰርቶ በማሳየት አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም በተሰሩት የፈጠራ ስራዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት የተካሂሄደ ሲሆን፣ የፈጠራ ስራዎቹ ከቤተ ሙከራ ወጥተው ወደ ማህበረሰቡ ለማድረስ ምቹ ሁኔታን ማመቻቸት እንደሚገባ በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡