በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በየአመቱ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በሁሉም ግቢዎች ይካሄዳል፡፡ በ2011 ዓ.ም ከወትሮው በተለየ መልኩ ከዩኒቨርሲቲው ግቢዎች በተጨማሪ ከግቢዎቹ ውጭ “አይራ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 5 ሄክታር ስፋት ያልው ቦታ ከጎንደር ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤትና ግብርና መምሪያ በመርከብ ሰኔ25/2011 ዓ.ም የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
በችግኝ ተከላው ፕሮግራም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይንን ጨምሮ ም/ፕሬዚዳንቶች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ ከጎንደር ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤትና ግብርና መምሪያ ተወካዮች ተሳታፊ ሲሆኑ፣12 ሺህ 2መቶ 75 ችግኞች እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡
በጎንደር ዩኒበርሲቲ የአየር ንብረት ለውጥ ምርምር አስተባባሪ ዶ/ር ኢብራሂም ኢሳ “የተተከሉት ችግኞች በቀጣይ ከፍተኛ የሆነ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸውና ቀደም ብሎ ጠባቂ እንደ ተመደበ” የገለጹ ሲሆን፣ በችግኝ የተሸፈነው 5 ሄክታር ቦታ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ገጠር ልማት ኮሌጅ፣ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ለደን ልማት ዲፓርትመንት ተማሪዎች የመስክ ምልከታ እና ምርምር አገልግሎት የሚውል መሆኑን ዶ/ር ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ተጨማሪ የችግኝ ቦታዎችን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር እንደሚረከቡም አክለው ገልጸዋል ፡፡