የሀዘን መግለጫ
የቀድሞው የዩኒቨርስቲያችን ባልደረባ የነበሩት ዶ/ር ዮናስ ጌታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩን ከልብ አዝነናል፡፡
ዶ/ር ዮናስ ጌታቸዉ ጥር 09/1965 በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸዉ ለትምህርት ሲደርስም በነጻነት ጮራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ 1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ከ 1970 እስከ 1977 ዓ.ም ተምረዋል፡፡
በሽመልስ ሃብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ከ1978 እስከ 1981 ተከታትለዋል፡፡በትምህርታቸዉ ጎበዝ ተማሪ ስለሆኑ ለኮሌጅ የሚያበቃ ዉጤት በማምጣታቸዉ ከ1982 እስከ 1988 በጎንደር ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል፡፡
ትምህርታቸዉን ካጠናቀቁ በጏላም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን በጠቅላላ ሃኪምነት በመጀመርያ በወናጎ ጤና ጣብያ ከዚያም በዲላ ሆሰፒታል ተመድበዉ ከ01/10/1988ዓ.ም እስከ 11/01/1991ዓ.ም ለ 2 ዓመት ከ2 ወር ያገለገሉ ሲሆን፣ የዲላ ሆሰፒታል ሜዲካል ዳይሬከተር በመሆንም በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡
እንዲሁም ከ 1991ዓ.ም ጀምሮ ወደ ጎንደር ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዝዉዉር በመጠየቅ በማህጸን እና ጽንስ ትመህርት ክፍል በረዳት ሌክቸረርነት ተቀጥረዉ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከ 1993 እስከ 1996 ዓ.ም የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊቲ ትምህርታቸዉን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምና ኮሌጅ ተከታትለዋል፡፡
ትምህርታቸዉን አጠናቀዉ ከተመለሱ ከመስከረም 1997ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም ከጎንደር ዩኒቨርስቲ እስኪለቁ ድረስ በረዳት ፕሮፌሰር ማእረግ የማስተማር ፣ የህክምና ስራና የማህጸን እና ጽንስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ዶ/ር ዮናስ ጌታቸዉ በዩኒቨርሲቲያችን በነበሩበት ወቅት በማህጸን እና ጽንስ ትምህርት ክፍል ሌላ የሚረዳቸዉ ሃኪም ባለመኖሩ አብዛኛዉን ጊዜ በብቸኝነት የህክምና እና የማስተማር ስራዉን ሁሉ በታታሪነት ሲሰሩ የቆዩ ከመሆናቸዉም በላይ ግለሰቡ እጅግ ርህሩህ፣ አዛኝ እና ጠንካራ ስብእና ያላቸዉ አርኣያ የሆኑ ታላቅ ሃኪም ነበሩ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የስራ ባልደረባ ሆነዉ እየሰሩ ባሉበት በዚህ ሰአት ባደረባቸዉ ህመም ምክንያት በጥቁር አንበሳ ሆሰፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተዉ በተወለዱ በ 47 ዓመታቸዉ ጥቅምት 17/2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ዩኒቨርስቲያችን በቀድሞ የስራ ባልደረባችን እና ሃኪማችን ህልፈት የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ፈጣሪ ነብሳቸዉን በአጸደ ገነት እንድያኖርልን እንመኛለን፡፡ ለቤተሰቦቻቸዉ እና ወዳጅ ዘመዶቻቸዉ መጽናናትን እንመኛለን፡፡
**************************************
ህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ጥቅምት 18/2013 ዓ.ም
