የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ‹‹ሰበዝ›› የተሰኘ መጽሔት ለምረቃ አብቅቷል
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀና በዓመት ሁለት ጊዜ የምትታተም ‹‹ሰበዝ›› የተሰኘች በአካዳሚያዊ፣ በማህበራዊ፣ በባህላዊ፣ በኪነ-ጥበባዊና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የምታደርግ መጽሔት የምረቃ ስነ-ስርዓት ዛሬ ሀምሌ 2/2013 ዓ/ም በማራኪ አልሙኒዬም ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡
በዚህ ስነ-ስርዓት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሰረት ካሴ፣ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አገኘሁ ተስፋ፣ መምህራንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

መርሐ ግብሩን የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አገኘሁ ተስፋ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያስጀመሩ ሲሆን በንግግራቸውም የመጽሔት ዝግጅት ባህል በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ተቋማት ደረጃ ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት በተለይም በዩኒቨርሲቲው መጽሔት የማሳተም ባህል እንዳልነበር አውስተዋል፡፡ አሁን ላይ ኮሌጁ ይህንን ሀላፊነት በመውሰድ መጽሔት ማሳተም መቻሉንና ወደፊትም ወቅታዊ የሆኑ ነገሮች እየተጠኑና እየተፃፉ ተቋሙ የሚሻሻልበት ህብረተሰቡም የሚገለገልበት መንገድ መፍጠር እንደሚገባ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ እንደ ሀገር በአስተሳሰብ የነቃ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራው ስራ ቀላል የሚባል እንዳልሆነና ከዚህ በላይም መስራት እንደሚጠበቅበት በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግራቸው የገለፁት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን በእለቱ የሚመረቀው ‹‹ሰበዝ›› የተሰኘ መጽሔት አንዱ ምእራፍ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ስራ ቀጣይነት እንዲኖረውና ሀገራዊ፣ ክልላዊ፣ አካባቢያዊ የሆኑ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች እንዲካተቱበትም ዶ/ር ሥራት የጠቆሙ ሲሆን፣ፕሮግራሙን ላዘጋጁና መጽሔቱ ላይ አሻራቸውን ያሳረፉ አካላትንም አመስግነዋል፡፡ ወደፊት ኮሌጁ ለሚሰራቸው ስራዎች የሚገባውን ሁሉ በማመቻቸት የተቋሙ አቅም እስከፈቀደ ድረስ እንደሚደግፉና ሌሎች ኮሌጆችም ተሞክሮውን መውሰድ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡ በመጨረሻም መጽሔቱን በይፋ በመክፈት አስመርቀዋል፡፡

በመቀጠል በመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ በመ/ር አስማማው አዲስ ስለ መጽሔቱ ዝግጅት ሂደት የተመለከተ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን አስተያየቶች ተሰጥቶበት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ዐበይት ክንውኖችን ማስተዋወቅና መሰነድ፣ መምህራንና ተማሪዎች ያላቸውን ግንኙነት ዘርፈ ብዙ እንዲሆን መምከር እና ማጠናከር፣ መምህራን በንባብና በምርምር ያላቸውን እውቀቶች የሚያካፍሉበት መንገድ ሆኖ ማገልገልን ዓላማ ያደረገ የመጽሔት ዝግጅት እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በመጨረሻም ለመጽሔቱ አዘጋጆች የምስክር ወረቀት በመስጠት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡
