የበየነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ስጋቶች እና መከላከያ መንገዶች ላይ ስልጠና ተሰጠ
በኢንፓክት አንፕሊፋየር ከሚደገፉ አለም አቀፍ ፕሮጀክቶች መሃል አንዱ የሆነው የበየነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ፕሮጀክት (Online Safety Project) በባህርዳርና በደሴ ከተሞች ከሃምሌ 10-11፣ 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ከሚገኙ 45 የመንግስት እና የግል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለተመረጡ 90 የአይ፥ሲ፥ቲ መምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱን የፕሮጀክቱ አሰተባባሪና የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ም/ዲን የሆኑት ዶ/ር ተስፋማሪያም ሙሉጌታ ገለጹ፡፡

የፕሮጀክቱ አላማ በአማራ ክልል የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች ስለበየነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ስጋቶች ማለትም የሃሰት መረጃ ፥ የጥላቻ ንግግር ፥ የገንዘብ ማጭበርበር ፥ የበይነ መረብ አካውንት ነጠቃ ፥ የወሲብ ንግድ ፥ ፆታዊ ትንኮሳ እና የአሸባሪዎች ምልመላ እና ስለመከላከያ መንገዶች ያላቸውን ግንዛቤ እና ተጋላጭነት ማጥናት፥ ግንዛቢያቸውን ማሳደግ እና በሁለተኛ ደረጃ የአይ፥ሲ፥ቲ ስርአተ ትምህርት የበየነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ስጋቶች እና መከላከያ መንገዶች እንዲካተቱ ማስገንዘብ መሆኑን ዶ/ር ተስፋማሪያም ገልፀዋል።

በመቀጠልም በስምንት ምራፎች የተከፈለ የማስለጠኛ ሞጁል መዘጋጀቱን እና ከመስከረም 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በሚገኙ 45 ትምህርት ቤቶች ለተመረጡ 3600 የሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች ስልጠናው እንደሚሰጥ ተገልፆል።

በስለጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ተወካይ አቶ ብርሃኑ በላይ ጉዳዩ አሳሳቢ እና ወቅታዊ መሆኑን በመግለፅ ከስልጠና የሚያገኙትን እውቀት እና ክህሎት እራሳቸውን እና ተማሪዎቻቸውን ከበየነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ስጋቶች እንዲጠብቁ ለሰልጣኞች አሳስበዋል፥ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ወቅታዊ የሆኑ ሃገራዊ እና ክልላዊ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠ የሚያደርገውን ጥረት በክልሉ ትምህርት ቢሮ ስም አመስግነው ጥርቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።