
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኪነጥበባትና ባህል ማዕከል የተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶችን አቀረበ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኪነጥበባትና ባህል ማዕከል (ኪባማ) የተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶችን ግንቦት 3/2015 ዓ.ም በማራኪ አሉምኒየም አዳራሽ ለታዳሚዎች አቀረበ፡፡
በኪነጥበብ ዝግጅቱ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እና በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የሚማሩ ተማሪዎች ተሳትፈዋል ፡፡ በእለቱ በተማሪዎች እና በአስተባባሪዎች የተዘጋጁ ቅኔአዘል መነባንቦች፣ግጥም፣ሙዚቃዊ ተውኔት እና ሌሎች አዝናኝና አስተማሪ ዝግጅቶች ለታዳሚዎች ቀርበዋል፡፡

በዝግጅቱ የተገኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አገኘሁ ተስፋ ፣ሰው ከኪነ ጥበብ ስለማስተዋል፣ፈጣሪን ስለመፍራት፣ስለ ማህበራዊ ተግባቦትና ሌሎች ጉዳዮች እንደሚማር አንስተው ፣ እንዲህ አይነት ዝግጅቶች ተማሪዎቸ ከቀለም ትምህርት ጎንለጎን ራሳቸውን እያዝናኑ ብዙ መልካም እሴቶችን እንዲገነቡ ያግዛሉ ብለዋል፡፡

የአካባቢው ባህል እንዲጠና እንዲሁም የጥበብ ተሰጥኦና ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ በማሰብ ወርሀዊ የኪነጥበብ ምሽቱ መዘጋጀቱን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኪነጥበባትና ባህል ማዕከል አስተባባሪ መ/ር መላኩ አለምነው አብራርተዋል፡፡
አንድነትን የሚሰብኩ፣ ታሪክና ባህላችንን የሚያጎሉ ዝግጅቶች የኪነጥበብ ምሽቱ ትኩረቶች ናቸውም ብለዋል፡፡ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን እንዲያውቅና በማንነቱ እንዲኮራ ኪነጥበብ ትልቅ ሚና እንዳለው የገለጹት መ/ር መላኩ፣ብዙ እንዳልተሰራ አንስተዋል፡፡ ስለሆነም በቀጣይ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለመገንባት በኪነጥበቡ ዘርፍ በሰፊው ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በኪነጥበብ ምሽቱ በኢትዮጵያ የሥነ-ተውኔት ታሪክ ከፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም ቀጥሎ ስማቸው በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ቀኝ ጌታ ዮፍታኄ ንጉሴ እና የጦር አርበኛዋ የጥበብ ሰው ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ተዘክረዋል፡፡
መሰል የኪነ ጥበብ ምሽቶች መዘጋጀታቸው ለተማሪዎች ዘርፈብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም ቀልድ አዘል በሆነ መልኩ ብዙ ቁም ነገሮችን እንዲማሩ እና እንዲሁም በፈተና እና በጥናት የተጨናነቀውን አእምሯቸው ለማዝናናት የኪነጥበብ ዝግጅቱን እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡
