ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በድምቀት አስመረቀ
የሰላሙ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ ማለትም ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም በድምቀት አስመረቀ፡፡
በዚህ ደማቅ የምረቃ ስነ ስርዓት የኢፌዴሪ የውኃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የበአሉ ልዩ የክብር እንግዳ የተከበሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ፣ የክብር ዶ/ር አርቲስት ቴወድሮስ ካሳሁን ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን ፣የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ ሞላ መልካሙ፣የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሀኑ ፈይሳ፣የቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የሳይንስና ከፍተኛ ት/ሚኒስቴር አማካሪ ፕ/ር መንገሻ አድማሱ ፣የተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት፣ የሐይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎች፣ የተመራቂ ወላጆችና ቤተሰቦች እንዲሁም የዕለቱ ተመራቂዎች ተገኝተዋል፡፡
በአመቱ በዩኒቨርሲቲው በተካሄደው በዚህ በሁለተኛው ዙር የተማሪዎች የምረቃ ስነ ስርዓት በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሀግብሮች ወንድ 4153 ሴት 2421 በአጠቃላይ 6574 ተማሪዎች በመጀመሪያ፣በሁለተኛ፣ በሶስተኛና በስፔሻሊቲ የትምህርት ደረጃዎች አስመርቋል፤እንዲሁም ለአንጋፋውና ፍቅር ሰባኪው የጥበብ ሊቅ አርቲስት ቴወድሮስ ካሳሁን የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቷል፡፡
የነገ የሀገራችን ተስፋ የሆኑ የዕለቱ ተመራቂዎች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ፈታኝ ሁኔታዎችን ሁሉ በጽናትና በታላቅ ጀግንነት ተቋቁመው ለዚች ልዩ ቀን በመድረሳቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን አስተላልፈዋል፡፡ ተመራቂዎቻችን ወረርሽኙ የፈጠረውን አዲስ ሁኔታ በመቋቋም ለዚህ መብቃታቸውም ልጆቻችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ተፈትነው ማለፍ እንደሚችሉ ከወዲሁ ያረጋገጠ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹትም በጎርፍ መጥለቅለቅ ለተጎዱ ዩኒቨርሲቲው የቻለው ድጋፍ አድርጓል ፤የወረታ ግብርና ኮሌጅን የሳተላይት ማዕከል አድርጎ ከፍቷል፤ 6ኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድ ብዙ ሰርቷል፤ እንቦጭን ለማስወገድ በርካታ ጥረት አድርጓል፤ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማርና ሀገራዊ ትስስርን የመፍጠር ስራ ተሰርቷል፤ በማይካድራና ሌሎች አካባቢዎች በተደረጉ ዘር ተኮር ጥቃቶች ላይ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጥናቶች እየተካሄዱ ነው፤ የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ይገኛል፣ እንዲሁም በገበታ ለሃገር ፕሮግራም ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በዲዛይን ስራ እና የጎርጎራ ከተማን መሪ እቅድ በማዘጋጀት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ በአጠቃላይ 54 የሚሆኑ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች መተግበራቸውን የገለፁት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በዚህ አመርቂ ተግባሩም ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ እውቅናና ሽልማቶች ከተለያዩ አካላት እንደተበረከቱለት በመክፈቻ ንግግራቸው አንስተዋል፡፡ “ከአባይ ወንዝ የምንቀዳው ፍቅር እንጅ ጥላቻ እንዳልሆነ ለተመራቂ ልጆቻችን በጓዳም በአደባባይም ነግረን አሳድገናቸዋል” በማለትም አለመግባባቶች በሰላም ይፈቱ ዘንድ በአባይ ተፋሰስ ለሚገኙ ሀገራት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢፌዴሪ የውኃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የበአሉ ልዩ የክብር እንግዳ የተከበሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ፣ እንደአድዋ በአንድ ያቆመን የአባይን ግድብን የውኃ ሙሌት በድል ባከናወንበት ወቅት በመካሄዱ የዛሬውን ምረቃ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ የራሳችንን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀማችንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማፍለቅና መጠቀም ባለመቻላችን በድህነት እንኖራለን፤ ለዚህ ደግሞ በእውቀት የተደራጀ ኃይል ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ፣ ስለሆነም ለትምህርት ትልቅ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ተመራቂዎች በትምህርት ህይወታቸው ያገኙትን እውቀት በራስ በመተማመን ስሜት ከሁሉም ጋር በመከባበርና በመስራት ታላቅ የሆነችውን ሀገር ታላቅነቷን ማስጠበቅ እንደሚችሉ ያላቸውን የጸና እምነት በመግለጽ ለተመራቂዎች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የእለቱ የክብር እንግዳ አያይዘውም የግድቡ ስራ አገር አቀፍና አለማአቀፍ ትኩረትና ድጋፍ እንዲያገኝና በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረገው ጉልህ ሚና ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ እውቅና ሰጥተዋል፡፡ ሁሉም ሰው በተሰማራበት ስራ መልካም ውጤት በማስመዝገብ ራስንም ሀገርንም የሚያስከብር መሆኑን ከድምጻዊ ቴወድሮስ ካሳሁን ሁሉ ሊማር ይገባል በማለት ለአርቲስት ቴወድሮስ፣ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡
ለተመራቂዎች፣ ለተመራቂ ወላጆችና ቤተሰቦች እንዲሁም ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት እንኳን ደስ አላችሁ!እንኳን ደስ አለን!