የአማራ ጥናት ተቋም
የአማራ ምድርና የአማራ ሕዝብ እጅግ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ተዝቆ የማያልቅ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሃብቶችን የተቸሩ ናቸው፡፡ እነዚህም ሃብቶች የበርካታ አካላት ትኩረትን የሳቡ በመሆናቸው ከጥንታዊ ግሪክ ጻሐፍት እስከ ዘመናችን ጻሐፍት ድረስ፣ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ጻሐፍት ድረስ እንዲሁም ከሐይማኖታዊ እስከ ዓለማዊ ጹሑፎች ድረስ በሰፊው ከትበውት ይገኛሉ፡፡
የአማራ ምድርና የአማራ ሕዝብ በበርካታ ምክኒያቶች የዓለምን ትኩረት የሳቡ ናቸው፡፡ የአማራ ሕዝብ የሚኖርበት የአፍሪካ ቀንድ የዓለምችን አንዱ የጅኦፖለቲካ ፋይዳቸው ጎልቶ ከሚታዩ ቦታዎች ውስጥ ነው፡፡ ከቀይ ባህር ጋር ያለው ቅርበትና የአባይ ወንዝ መነሻ እንዲሁም ለወንዙ ብዙውን የውሃ ድርሻ የሚያበረክቱ ወንዞች ባለቤት መሆኑ አንዱ የዓለምን ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው፡፡ በተጨማሪም ከጥንት ከሲራራ ንግድ ጊዜ ጀምሮ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ የሚሳለጥበት አካባቢ በመሆኑ በምጣኔ ሃብትና በስልተምርት ያለው አስተዋፅኦ ጉልህ ነበረ፡፡ በዘመናችን ደግሞ የተለያዩ የግብርና ምርቶች በስፋት የሚመረቱበትና አያሌ የከበሩ ማዕድናት መገኛ አካባቢ በመሆኑ አሁንም ቢሆን የምጣኔ ሃብት የትኩረት ማዕከል ሁኖ እየቀጠለ ይገኛል፡፡
የአማራ ሕዝብ በርካታ ኪነ-ጥበባዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ሃብቶች ባለቤት ነው፡፡ ከኪነ-ጥበባዊ ሃብቶች መካከል የስነ-ጹሑፍ፣ የስነ-ስዕል፣ የቅርፃ ቅርፅ፣ የባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች፣ የውዝዋዜ፣ የቲያትር፣ የፊልም እንዲሁም የዕደ-ጥበብ ውጤቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከባህላዊ ሃብቶች መካከል የሰርግ፣ የሀዘን፣ የሽምግልና፣ የፍትህ፣ የልጅ አስተዳደግ፣ የትምህርት፣ የጉርብትና፣ የማህበር፣ የእድር፣ የእቁብ፣ የውበት አጠባበቅ፣ የአካባቢ እንክብካቤ፣ የምህንድስና፣ የስርዓተ ፆታ፣ የመድሐኒትና ህክምና፣ የግብርና፣ የአመጋገብ፣ የአለባበስ እና የመሳሰሉት እድሜ ጠገብ ሃብቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከኪነ-ጥበባዊ እና ከባህላዊ ሃብቶች ባላነሰ ህዝብ ዳጎስ ያለ አገረ መንግስትን መመስረትና አገርን የማፅናት ታሪክ ባለቤት ነው፡፡
የአንድን ማህበረሰብ ባህልን፣ ታሪክን፣ ቋንቋን እና ሌሎች እሴቶችን ለይቶ፣ ሰብስቦ፣ ቀርሶና ተንትኖ ለጥቅም ማዋል የሁሉንም የጥናትና የትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎች የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ፣ ተከታታይነት ያለው እና ተቋማትን አደራጅቶ መንቀሳቀስን የሚሻ ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ የአማራ ምድርንና የአማራ ሕዝብን ዋና ጉዳዩ አድርጎ በተቋም ደረጃ የሚንቀሳቀስ ተቋም እስካሁን የለም፡፡
ከዚህ በመነሳት ለአማራው አካባቢና ለአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ እድገት በተቋማት የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ የአማራን ምድርንና የአማራ ሕዝብን የሚገልጹ ቁሳዊና መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ሐይማኖታዊ፣ ማህበራዊ፣ ታሪካዊና አሁናዊ እንዲሁም ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ የሆኑ የማንነቱ መገለጫ ሃብቶችና ጉዳዮች በሙሉ ተጠብቀው የአሁኑ ትውልድም ሆነ መጭው ትውልድ እንዲጠቀምባቸው እና ዋጋቸውን በአግባቡ ተረድቶ ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲያሸጋግራቸው በተደራጀ መልኩ መምራት ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ይህ የአማራ ጥናት ተቋም ይህንን ውዴታም ግዴታም የሆነ ኃላፊነት ለመወጣት የዳሰሳ ጥናትና አውደ ጥናት ተደርጎ ሚያዚያ 24፣2015 ዓ.ም. ተቋቋመ፡፡
ራዕይ
2027 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ የአማራ ምድርና የአማራ ሕዝብ የስልጠናና ምርምር የልህቀት ማዕከል ሆኖ ማየት
ተልዕኮ
የአማራ ህዝብ ባህልን፣ ትውፊትን፣ ታሪክን፣ ኪነ-ጥበብን፣ የስነ-ልቦና ስሪትን፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሃብቶችን፣ ሳይንሳዊ አበርክቶዎችን ለመመርመርና ለማጥናት፣ ለመጠቀምና ሰንዶ ለማቆየት እንዲቻል ግንዛቤ መፍጠር፣ ብቁ ባለሙያዎችን ማሰልጠንና ማፍራት የተቋሙ አንዱ ተልዕኮ ነው፡፡ ተቋሙ በተለያዩ ዘርፎች ለተመራማሪዎች፣ ለሙሁራን እና ለባለሙያዎች ትብብር የሚያደርጉበት እና ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲለዋወጡ የሚያስችል መድረክ ሁኖ እንዲያገለግል ማድረግም ሌላው ተልዕኮ ነው፡፡
ዓላማ
አጠቃላይ ዓላማ
የአማራን ምድርና ህዝብ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን በተደራጀ ሁኔታ ማጥናት፣ መመርመር፣ መሰነድና ለጥቅም ማዋል
ዝርዝር ዓላማዎች
• የአማራን ምድርና ህዝብ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን ላይ ትኩረት ያደረጉ የትምህርት ፕሮግራሞችን መቅረፅና መስጠት፤
• የአማራን ምድርና ህዝብ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ፤
• የአማራን ምድርና ህዝብ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን ላይ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በትምህርታዊ መጽሔቶች ላይ ማሳተም፤
• የአማራን ምድርና ህዝብ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን ላይ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን የሚታተሙበት መጽሔት ማቋቋም፤
• ከአማራ ምድርና ህዝብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጻሕፍት፣ የብራና ጽሑፎች እና ሌሎች ሰነዶችንና የህትመት ውጤቶችን የሚይዝ አካታች ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ-መዛግብት ማቋቋም፤
• የአማራን ምድርና ህዝብ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮችን ላይ የማማከር አገልግሎት መስጠት፤
• አማርኛን የሳይንስ ቋንቋ ማድረግ
• የአገራችንን የተለያዩ ቋንቋዎች በኢትዮፒክ ስክሪፕት (በአማርኛ ፊደላት) ማስተማርና ስልጠና መስጠት፤
የተቋሙ መሪ ቃል
ማህበረሰቡን ለማገልገል እንተጋለን!
የተቋሙ እሴቶች
ልህቀት፡- ተቋሙ በሁሉም ተግባራቱና እንቅስቃሴው የላቀ ሙያዊ እሴትን የጠበቀ ይሆናል፡፡
ከወገንተኝ ነፃ፡- ተቋሙ ከርዕዮተ ዓለም፣ ከሐይማኖት፣ ከፖለቲካ እና ከሌሎች ጉዳዮች ወገንተኝነት ነፃ ነው፡፡
ፋይዳ፡- ተቋሙ የአማራ ህዝብ ጉዳይ ላይ ለሚነሱ አርዕስቶች የአጭርና የረጅም ጊዜ ለፖሊሲ ቀረጻና ለሌሎች ፍላጎቶች ግብዓት የሚሆኑ ጠቃሚና ተገቢ ሃሳቦችን በማቅረብ ፋይዳ ያለው ተቋም ይሆናል፡፡
ራስ ገዝነት፡- ተቋሙ ከማህበረሰቡ እና ከተለያዩ ድርጅቶች የሚያገኘውን የተለያዩ ድጋፎች እንዳሉ ሁነው ከየትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊና አስተዳዳራዊ ተዕፅኖ ነፃ ሁኖ ዓላማዎቹን ያሳካል፡፡
አገራዊነትና ዓለም አቀፋዊነት፡- ተቋሙ የአገራችንና የዓለም አቀፍ ሙሁራንን ያቀፈ አደረጃጃት ሲኖረው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር የአማራ ህዝብ ጉዳዩች ላይ ሙሁራዊ ጥምረትን በፈጠረ መልኩ በትብብር ስራዎችን ይመራል፡፡
ቁርጠኝነት፡- ተቋሙ እንደ ዓላማ ይዟቸው የተነሳባቸውን ጉዳዮች ከግብ ለማድረስ በሙሉ ቁርጠኝነት ይሰራል፡፡
ዘላቂነት፡- ተቋሙ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ተጀምሮ የሚቀሩ ሳይሆን በዘላቂነት ለህዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን ያከናውናል፡፡
የአማራ ጥናት ተቋም ተቋማዊ መዋቅር አደረጃጃት መግለጫ
የአማራ ጥናት ተቋም ተጠሪነቱ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነው፡፡ ከፕሬዚዳንቱ በመቀጠል ተቋሙን በባላደራ ቦርድ በበላይነት የሚመራው ሲሆን ባላደራ ቦርዱም ተጠሪነቱ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሆኖ የተቋሙን ዳይሬክተር በሃላፊነት ይመራል፣ ይቆጣጠራል፣ ያስተዳድራል፡፡ የባላደራ ቦርዱ አባላት የሚመረጡት በዩኒቨርሲቲው ፕሬዜዳንት ሲሆን የአባላቱ ስብጥርም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ፣ ከዩኒቨርሲቲው ውጭ፣ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ የተቋሙን እሴቶችና ዓላማዎች የሚደግፉና የሚያስቀጥሉ ግለሰቦች ይሆናሉ፡፡ እንደአስፈላጊነቱ ተቋማትም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአባላቱም ብዛት ከ7 እስከ 11 ይሆናሉ፡፡
በተቋሙ ስር የሚገኙ ማዕከላት
ይህ ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ነው፡፡ የአገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአማራ ምድርንና የአማራ ህዝብን ጉዳዮችን በተመለከተ አሁን ስልጠናዎችን እየሰጡበት ካለው በተለየ እና በሰፋ መልኩ በትብብር ስልጠናዎችን የሚሰጥ ማዕከል ሲሆን ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ ስርዓተ ትምህርቶችን በመቅረፅ እና ከጊዜ እድገት ጋር አብሮ የሚመጡ ተለዋዋጭ ጉዳዮች በአንክሮ በማጤን የአማራ ህዝብ ከራሱ አልፎ ለአገራችን እና ለዓለማችን ያበረከተውን አስተዋፅኦ በከፍተኛ ትኩረት እና በስፋት የሚመረምርና የሚያጠና ለጥቅም የሚያውል ማዕከል ነው፡፡
ማዕከሉ በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎችና ተቋማት ጋር በመተባበር ስልጠናዎችን እና ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ በሰርተፊኬት፣ በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያ ዲግሪና በድህረ ምረቃ ደረጃዎች ከየትኛውም የዓለም ክፍል ለመጣ ደንበኛ በሙሉ ይሰጣል፡፡
ይህ ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ሲሆን ማዕከሉ የአማራ ህዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ እና ሌሎች አያሌ አገር በቀል ጉዳዮችን ለማጥናት፣ ሰንዶ ለማቆየትና ጥቅም ላይ ለማዋል የጥናትና ምርምር ተግባራትን በልዩነት ያከናውናል፡፡
በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚመጡ ተመራማሪዎችና አጥኝዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የልማት ወኪሎች እንዲሁም ሌሎች በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ለማጥናት ቢፈልጉ የተደራጀ እና ተደራሽ የሆነ የጥናት እና ሌሎች ተዛማጅ ጹሑፎች ተደራጅተው የሚገኙበት ማዕከል ነው፡፡ ይህ ማዕከልም በአጋርነትና በትብብር ጥናትና ምርምር ያከናውናል፡፡
የዚህም ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ሲሆን የአማራ ሕዝብ ጉዳዮችን ዋና ትኩረታቸው ያደረጉ የትኛውንም አይነት አካዳሚያዊም ይሁን ከአካዳሚያዊ ውጭ የሆኑ ጹሑፎችን በመልክ በመልኩ በማደራጀት ለዓለም ተደራሽ በማድረግ የአማራን ምድርና ሕዝብ ህልውና ተጠብቆ እንዲቆይ የሚደርጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶቸን ማሳተም ዋና ተግባሩ ሲሆን በሂደትም ራሱን የቻለ ታዋቂ ትምህርታዊ መጽሔት/ጆርናል ይመሰርታል፡፡
ይህ ማዕከል በአማራ ምድርና ህዝብ ዙሪያ የሚያተኩሩ የተዛነፉ እና የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ሁሉንም ዓይነት የህትመት ውጤቶችን በመለየት የማስተካከያ ግብረ መልስ የሚሆኑ ጥናቶችን ያደራጃል፡፡
ይህ ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ነው፡፡ ማዕከሉ የተቋሙን የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን የሚሰራ ማዕከል ነው፡፡ በተጨማሪም የአማራን ህዝብ ኪነጥበብ፣ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜ፣ ቲያትር እና ሲኒማ የሚታይበት መድረክና ይህንን መድረክም የሚያስተባብር፣ የሚያደራጅና የሚመራ ማዕከል ነው፡፡
ይህ ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ነው፡፡ የአማራና የአማራ ህዝብ ጉዳዮችን የሚያወሱ ቤተ-መጻህፍትና ቤተ-መዛግብት በማቋቋም መጻህፍቶችን፣ መጽሔቶችን፣ ጥንታዊ ጹሑፎችን እና ሌሎች የህትመት ውጤቶች በአግባቡ ተጠብቀው ለመጭው ትውልድ ለማቆየትና የህዝብን የንባብ ባህል ለማሳደግና ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡
በተጨማሪም ማዕከሉ ሙዚየም የሚያቋቁም ሲሆን ሙዚየሙ ለተመራማሪዎች የመረጃ ምንጭ፣ ለተከታታይ አዲስ ትውልዶች የማንነታቸው መመልከቻ፣ የባህልና የታሪካቸው መማሪያና ማስረጃ ትምህርት ቤት ይሆናል፡፡
አጋር አካላት





-
ዶ/ር በዛብህ ተስፋሁነኝ
- Tel (phone): +251944711180
-
Amhara.Studies@uog.edu.et
alemyebeza@gmail.com - የተቋሙ ዳይሬክተር