
’’ሀገር በቀል የትብብር ፒ ኤች ዲ ፕሮግራሞች እና አካታች የምርምር ቡድኖች ’’ (Home- Grown Collaborative PhD Programs and 20 New Interdisciplinary Research Groups) በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት አዘጋጅነት ’’ሀገር በቀል የትብብር ፒ ኤች ዲ ፕሮግራሞች እና አካታች የምርምር ቡድኖች ’’ (Home- Grown Collaborative PhD Programs and 20 New Interdisciplinary Research Groups) በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ ዲኖችና ዳይሬክተሮች እንዲሁም ከሌላ ዩኒቨርሲቲዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ሰኔ 2/2013 ዓ.ም በማራኪ ግቢ አልሙኒየም አዳራሽ ውይይት ተካሄደ፡፡

በውይይት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በዩኒቨርሲቲያችን አዲስ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት ሁላችንም በአንድነት ከተባበርን ተቋማችንን ችግር ፈች የምርምር ተቋም ማድረግ እንችላለን ብለዋል፡፡ አያይዘውም ሃሳቡን በማመንጨት ፕሮግራሙን ላዘጋጁ ለምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ለዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ እንዲሁም ለክፍሉ አባላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲያችን የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ከምርምር ፈንዶች ጋር በቅንጅት እንዴት መስራት እንደሚችል እና ስለ አገር በቀል 3ኛ ዲግሪ ትብብር ፕሮግራም የሚያስገነዝብ ገለጻ ያደረጉት የድህረ ምረቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አለሙ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሃገራችን እድገት ለማፋጠን በሚቀጥሉት አምስት አመታት በተመረጡ አምስት ዲፓርትመንቶች ብቃት ያላቸው 5000 ተማሪዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማፍራት መታቀዱን የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም አንደምርምር ዩኒቨርሲቲ የፒ ኤች ዲ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው የሚያባክኑትን ረዥም ጊዜ በአጭር ጊዜ ውጤታማ ጥናቶች የሚሰሩበትን ሁኔታ መዘርጋት እና ምርምርና ድህረ ምረቃን በቅንጅት መስራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡ አንዲሁም ጠቃሚ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ምርምር የሚሰሩ የፒ ኤች ዲ እና ማስተርስ ተማሪዎችን ያካተተ 20 የሚሆኑ አዳዲስ የምርምር ቡድኖች ለመመስረት መታቀዱንም አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም የማህበረሰብ አገልግሎት መመሪያ፣ የምርምርና ህትመት ፣ የዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጅ ሽግግር እንዲሁም የምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጅ ሽግግር የትኩረት አቅጣጫ /Thematic Area/ ላዘጋጁ ኮሚቴ አባላት የእውቅናና የሽልማት ስነ-ስርአት ተካሂዷል፡፡




