’’ሁለገብ የመኖ እጽዋት ስልታዊ ልማትና የእንስሳት አመጋገብ’’ በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት እርባታና ስርፀት ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት ’’ሁለገብ የመኖ እጽዋት ስልታዊ ልማትና የእንስሳት አመጋገብ’’ በሚል ርዕስ በምእራብና በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ከተለያዩ ቀበሌዎች ለተውጣጡ አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች በቆላድባ ከተማ ግንቦት 21/2013 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ ፡፡

“ምንም እንኳን ጠባብ ቦታ ቢኖራችሁም ጭብጥ እርጥብ መኖ አምርቶ ለከብቶች በመመገብ ጤናቸው ተጠብቆ ምርትና ምርታማነታቸውን መጨመር ይቻላል” ሲሉ የእንስሳት ህክምና ማህበረሰብ አገልግሎት ተወካይ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው የተሰጠው በትምህርት ክፍሉ መምህራን ሲሆን ዋና አላማውም የመኖ እፅዋት ልማት ዘዴዎችን ማስተዋወቅ፣ ሁለገብ የመኖ ምርት ስልታዊ በሆነ መንገድ አልምቶ እንስሳትን በመመገብ በሀገራችን ምርትና ምርታማነትን መጨመር እና በተለያዩ ምክንያቶች የተመናመነውን የግጦሽ መሬት መጠን ለመጨመር እንደሆነ የእንስሳት እርባታና ስርፀት ትምህርት ክፍል መምህርና የስልጠናው ዋና አስተባባሪ አቶ አስማማው ይነሱ ገልጸዋል፡፡




