ለባዮ-ሜዲካል ሙያተኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በባዮ ሜዲካል ኢንጅነሪንግ የትምህርት ዘርፍ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር በኩል በክልሉ ቀዳሚ እንደሆነ ይታወሳል፡፡

ት/ት ክፍሉ ኮፊ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የኮሪያ የጤና ድርጅት (KOFIH – Korea Foundation for International Health) ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ጤና ቢሮ በኩል ተመልምለው የመጡ የባዮ ሜዲካል ሙያተኞችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡

ሰልጣኞችን እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን መስፍን፣ ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት አቶ ሰሎሞን ፋናታው (የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር) እና የዩኒቨርሲቲው ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አካዴሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ ለሰልጣኞች እንደየ ቅደም ተከተላቸው መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡

ሀገራችን ከውጪ ከምታስመጣቸው ቁሳቁሶች መካካል ለጤናው ዘርፍ ግልጋሎት የሚውሉት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ይደረግባቸዋል ያሉት የትምህርት ክፍሉ ኃላፊና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ብሩህ ተስፋ ሙሀባው ናቸው፡፡ በመሆኑም በሀገር ደረጃ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ፣ በስራ ላይ ብልሽት የሚያጋጥማቸውን የህክምና ቁሳቁሶች ለመጠገንም ሆነ አጠቃቀማቸውንም ይበልጥ ለመረዳት ይቻል ዘንድ፣ ለዘርፉ ሙያተኞች ስልጠናው መዘጋጀቱን አቶ ብሩህ ተስፋ አያይዘው ተናግረዋል፡፡ ስልጠናው ለአንድ ሳምንት እንደሚቆይና ለሌሎች ሙያተኞች በተመሳሳይ በሌሎች ዙሮች ተደራሽ እንደሚሆን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የባዮ ሜዲካል ሙያተኞች ከዚህ በፊት በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የህክምና ቁሳቁሶችን የመጠገን ስራ መስራታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ባ/ዳር አዲስ ዓለም ሆስፒታል፣ ደ/ታቦር ሆስፒታል፣ ደባርቅ ሆስፒታል፣ እንጅባራ ሆስፒታልና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑ ሆስፒታሎች መካካል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡



