
ለባዮ ሜዲካል ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪዎች ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት የባዮ ሜዲካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል “ክሊንተን ኸልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ” ከተሰኘ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ለ2013ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዝቃዛ ሰንሰለት (Cold Chain) ላይ በሚሰሩ ባለሙያዎች አማካኝነት ከሀምሌ 26/2013ዓ/ም ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚቆይ በቀዝቃዛ ሰንሰለት (Cold Chain) ላይ ያተኮረ በተግባር የተደገፈ ስልጠና በኢኒስቲቲዩቱ የስልጠና ማእከል በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ በተግባር የተደገፈ ስልጠና መሰጠቱ ተመራቂዎች ተወዳዳሪነታቸውን በመጨመር፣ የስራ ብቃታቸውን ከፍ በማድረግ ተመራቂዎች ተመራጭ እንዲሆኑ ማስቻልን አላማ ያደረገ መሆኑን የትምህርት ክፍሉ መምህርና የኢኒስቲቲዩቱ የኢንዱስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር አስተባባሪ መ/ር ብሩህተስፋ ሙሀባው ገልፀዋል፡፡ ስልጠናውን እየሰጠ የሚገኘው ድርጅት ከስልጠናው በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የጋራ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙንና ስልጠናው እየተሰጠበት ያለውን ክፍል በቋሚነት የስልጠና ማዕከል ሆኖ ማገልገል እንዲችል ወደፊት ቁሳቁሶችን እንደሚያሟሉ ቃል መግባታቸውን መ/ር ብሩህተስፋ አክለው ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም መ/ር ብሩህ ተስፋ ዩኒቨርሲቲው ይህንን ስልጠና እንዲሰጥ በማመቻቸቱ ያላቸውን አድናቆት የገለፁ ሲሆን፣ በሌሎች የትምህርት ክፍሎችም ተወዳዳሪ የሆኑ ተመራቂዎችን ለማፍራት መሰል ስራዎች እንዲሰሩ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አበክረው ተናግረዋል፡፡
ቀዝቃዛ ሰንሰለት ( Cold Chain) በሚል ርእስ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ክትባት ጉዳት ሳይደርስበት ከተመረተበት ቦታ እስከሚሰጥበት ድረስ በሚፈለገው የቅዝቃዜ መጠን ውስጥ ሆኖ እንዲደርስ የቀዝቃዛ ሰንሰለት ቁሳቁሶችን ጥገና ተመራቂዎቹ እንዲያውቁትና ወደ ስራ ሲገቡ በአግባቡ እንዲሰራ ለማድረግ አላማ ያደረገ ስልጠና እንደሆነ በጂማ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ሜዲካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ኃላፊና አሰልጣኝ የሆኑት መምህር ሁንዴሳ ዳባ ገልፀዋል፡፡ ተመራቂዎች ይህንን ስልጠና ማግኘታቸው ተጨማሪ ክህሎት ኖሯቸው በስራ መስኩ ላይ የሚያጋጥሟቸውን አንዳንድ የጥገና ችግሮችን ለመቅረፍ የተሻለ እውቀት ይዘው የተሻለ ስራ መስራት አንዲችሉ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡
ይህ ስልጠና በዋናነት 39 ለሚሆኑ የባዮ ሜዲካል ትምህርት ክፍል የ2013ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች እየተሰጠ እንደሚገኝና በተጨማሪም ለ4ኛ አመት ኢንተርን ሽፕ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች እንዲሁም ለሜካኒካል ትምህርት ክፍል ቴክኒካል ረዳቶች እየተሰጠ እንደሚገኝ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡