ለተሻለ የግብርና ስርፀት የባለድርሻ አካላት ትስስር በሚጠበቀው ልክ ተግባራዊ አለመደረጉ ተገለፀ
የአርሶ አደሩን ችግር መነሻ በማድረግ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በቀረበ የጥናት ልየታ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ በ5 ወረዳዎች ያደረገውን የጥናት ውጤት፣ በቆላድባ ከተማ ከዞን እሰከ ቀበሌ ከሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ባለሙያዎችና አመራሮች ጋር በተካሄደ የምክክር መድረክ “የተሻለ የግብርና ኤክስቴንሽን ስርጸትን ለማምጣት የአጋር አካላት ቅንጅት ምን ይመስላል” በሚል የጥናት ውጤቱ በኮሌጁ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ፣ መምህርና ተመራማሪ በሆኑት በአቶ በየነ ደርሶ አማካኝነት ቀርቧል፡፡
በቀረበው የጥናት ውጤት ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በዓይነት፣ በብዛት እና በጥራት ለማምረት የሚያስችል ሀብት እና ምቹ ተፈጥሮአዊ ስነምህዳር ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህንን ሀብትና ምቹ ሁኔታ በአግባቡ በመጠቀም ሀገሪቱ በምግብ ራሷን እንዲትችልና ከዚያም አልፎ ለሌሎች ሀገራት እንድትተርፍ ለማስቻል የአርሶ አደሮችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም በማሳደግ ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል የኤክስቴሽን ስራን በሰፊውና በትኩረት መስራት ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት ደግሞ የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ቢሆንም ትግበራው ግን በሚጠበቀው ልክ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡
እነዚህ ባለድርሻ አካላት እነማን ናቸው፣ ሚናቸውስ ምንድነው? ቅንጅታቸውና ትስስራቸው በምን መልኩ መሆን አለበት እንዲሁም የአጋር አካላት ቅንጅት ጠንካራ እንዳይሆን ያሉ ተፅእኖዎች ምን ምን ናቸው የሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች በጥናቱ ተዳስሰዋል፡፡
ከጥናት ውጤቱ በተጨማሪ በግብርና ኤክስቴንሽን መርሆዎችና ተያያዥ በሆኑ ሀሳቦች ዙሪያ በኮሌጁ መምህራን በወ/ሮ ሀገሬ በላቸው እና በደ/ር ክብሮም አድኖ አማካኝነት ገለፃ ቀርቧል፡፡ የጥናት ውጤቱንና ገለፃውን ተከትሎ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ለቀረቡ ጥያቄዎችም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ምክትል ዲን ዶ/ር ተፈሪ አለሙ፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የቀበሌ ግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጥሪ የተደረገላቸው ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም አርሶአደሮች የተገኙ ሲሆን ጥናቱ በክልል ደረጃ ለሚገኙ አመራሮችና ባለሙዎች ቀርቦ ግንዛቤው መያዝ እንዳለበትና ሁሉም አመራርም ሆነ ባለሙያ ለግብርና ስርፀቱ በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ በመሆንና ትኩረት በመስጠት ለተሻለ ውጤት መሰራት እንዳለበት በመግባባትና ቀጣይ አቅጣጫዎችም በማስቀመጥ መርሀግብሩ ተጠናቋል፡፡ ተመሳሳይ ውይይት በወገራ ወረዳ እንደሚቀጥል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡