ለትጉህ ማህበር አባላት መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብት ማእከል ጋር በመተባበር በመሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ ዙርያ ለትጉህ(ትብብር ለጉዳተኞች ህይወት) ማህበር አባላት ከህዳር30 እስከ ታህሳስ 01/2013ዓ/ም በህግ ትምህርት ቤት ምስለ ችሎት አዳራሽ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ በህገ- መንግስት የምትተዳደር ሀገር ከመሆኗም በላይ በርክታ የፈረመቻቸው የሰብአዊ መብት ስምምነቶች እና በአለምአቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታት ጥላ ስር የሚተዳደሩ ሰብአዊ መብቶችን የሚጠብቁ ድርጅቶች ያወጧቸን መመሪያዎች የተቀበለች ቢሆንም ከሶስት አስርት አመታት ወዲህ ግን አሰቃቂ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል ያሉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ፣ የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ለሆኑት ለትጉህ ማህበር አባላት ስልጠና እንዲሰጥ ያደረጉ አዘጋጆችን በፕሮግራሙ መክፈቻ ንግግራቸው አመስግነዋል፡፡ በንግግራቸውም ሰልጣኞች ሰብአዊ መብቶችን በማክበር፣ ሰብአዊ መብት እንዲከበር፣ ስርአት እንዲገነባ ጥረት በማድረግ ለሌሎች በማስተማር የሰብአዊ መብቶችን ጥሰት ለመከላከል የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ስልጠናው በመሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች፣ በመሰረታዊ የፖለቲካና ሲቪል መብቶች፣ በሰብአዊ መብቶች የማስፈ ፀሚያ ስነ-ስርአቶች፣ የሲቪልና የበጎ አድራጎት ማህበራት ህግ ዙሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ የትምህርት ክፍሉ ተጠባባቂ ዲን ዶ/ር ሰለሞን ተክሌ በነፃ የህግ አገልግሎቱ አስተባባሪ በአቶ ደሞዝ ካሴ ፣ እና በአቶ በለጠ ካሴ ተሰጥቷል፡፡
አሁን ባለው የሀገራችን ሁኔታ ከጊዜ ጊዜ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተበራከተ የሚታይበት ወቅት መሆኑን ዶ/ር ሰለሞን ተክሌ ያወሱ ሲሆን፣የተለያዩ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲከበሩ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እና መንግስት ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ሰለሞን አያይዘውም በአንድ ሀገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሊፈጠር የሚችለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝን ማሻሻል ሲቻል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ስልጠናም የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነድ በፀደቀበት ታህሳስ 1 ቀንን ታሳቢ ያደረገ ስልጠና እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ስልጠናው ሰብአዊ መብቶች እንዴት ተፈፃሚ እንደሚሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ሰልጣኞች ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች የማስገንዘብ ስራ የመስራት፣ የማህበር አባላት እንደመሆናቸው ማህበሩን ለማገዝ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውና ከስልጠናው በተጨማሪ የነፃ የህግ አገልግሎት መዋቅሩን በመጠቀም የህግ ምክር፣ የማመልከቻ የማፃፍ፣የጠበቃ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ የማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ደሞዝ ካሴ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም በህግ ትምህርት ቤት ተጠባባቂ ዲኑ በዶ/ር ሰለሞን ተክሌ የመዝጊያ ንግግር እና የወደፊት አቅጣጫዎች ተሰጥተው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡********************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 01/2013 ዓ.ም







