ለንብ አናቢዎችና ለግብርና ሙያተኞች የስራ ላይ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎቶች አሁንም ተጠናክርው እየቀጠሉ ይገኛሉ፡፡ በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ከ200 ኪ/ሜትሮች በላይ በመጓዝ በእንስሳት ሀብት፣ በሰብል ልማትና በተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ለጃን አሞራና ለበየዳ ወረዳ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና የግብርና ሙያተኞች የስራ ላይ አቅም ማጎልበቻ ስልጠና መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ በተጠቀሱት ወረዳዎች ለሚገኙ ከ 80 በላይ ለሚሆኑ ንብ አናቢዎችና ለ 16 የግብርና ሙያተኞች፣ የንብ ሀብት ልማትን ማሻሻል፣ ንቦችን ማባዛት እንዲሁም ከባህላዊ ወደ ዘመናዊና ሽግግር ቀፎ በማዘወር የህብረ-ንብ ቁጥርን መጨመርና ምርታማነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ የስራ ላይ ስልጠና በድል-ይብዛ ከተማ ከጥር 20 – 21/2012 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አዲስ ጌጡ፣ የበየዳ ወረዳ የእንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፋያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉየ አዲሴ፣ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያላቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራን፣ አርሶ አደሮችና የግብርና ሙያተኞች በስልጠናው በንቃት ተሳትፈዋል፡፡

የሰሜኑ ወረዳዎች (በየዳና ጃን አሞራ) በነበረባቸው የመሰረተ ልማት ችግሮች ምክንያት ህብረተሰቡ በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በስፋት እንዳይጠቀም እንቅፋት ሁኖ ቆይቶ ነበር ብለዋል አቶ ሙልየ፣ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው፡፡ አቶ ሙልየ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ በሳይንስ የተደገፉ የጽንሰ-ሀሳብና የተግባር ስልጠናዎችን መስጠት በመቻሉ በአርሶ አደሩ ዘንድ የስራ መነቃቃት እንደተፈጠረ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አዲሱ በመክፈቻ ንግግራቸው ወረዳዎቹ ያላቸው ተፈጥሮ ለንብ ሀብት ልማት ምቹ መሆኑኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ የስራ ዘርፍ እንደ ሌሎች የግብርና ዘርፎች ሰፊ የቦታ ይዞታ፣ ብዙ የገንዘብና የጉልበት ወጪ እንደማይጠይቅ አስተባባሪው ገልጸው፣ አናቢዎች ይህንን እንዲረዱ ለማድረግና ያለባቸውን ክፍተት በተግባር በማሳየት ከዘርፉ ማግኘት እሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ማስቻል የስልጠናው ዋና አላማ መሆኑን አቶ አዲሱ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
፲ አለቃ አዛኔ ነጋ ነወሪነታቸው በየዳ ወረዳ ዋቲ ቀበሌ ሲሆን ንብ በማነብ ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ልጆቻቸውን ከማስተማር ባለፈ ወደ አርሶ-አደሩ ወርዶ እየሰራቸው ባሉ ሁለ-ገብ ስራዎች ከልብ መደሰታቸውን ፲ አለቃ አዛኔ ከስልጠናው በኋላ ገልጸውልናል፡፡



