ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያንና ለተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች የገቢ ማስገኛ የሚሆን የእህል ወፍጮ ፕሮጀክት ተመረቀ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አቀፍ መልሶ ማቋቋም(CBR) ላይ አርማጭሆ ወረዳ ለሚኖሩ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያንና ለተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች የገቢ ማስገኛ የሚሆን የእህል ወፍጮ በመግዛት አገልግሎቱን ለማስጀመር ጥር 6/2012 ዓ/ም በትክል ድንጋይ ከተማ የፕሮጀክት ምረቃ ስነ-ስርአት ተካሄደ፡፡

በዕለቱ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ማለደ፣ የወረዳው መሪ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ቀናው ጌጡ፣ የወረዳው የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ወርቄ ከበደ፣ የዩኒቨርሲቲው ሲቢአር አስተባባሪ አቶ ሰሎሞን ዳውድ፣ ከማእከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ እና ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ከከተማው ነዋሪዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

የወረዳው መሪ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ቀናው ጌጡ የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ፕሮግራሙን ያስጀመሩ ሲሆን፣ በንግራቸውም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲቢአርን ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያንና ለተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች የስራ እድል ለመፍጠር እና ለማቋቋም ያደረገውን 310,000.00 (የሶስት መቶ አስር ሽ) ብር ድጋፍ በወረዳው ህዝብ ስም አመስግነዋል፡፡ አቶ ቀናው አያይዘውም ይህንን አርአያነት ያለውን ስራ እንደመነሻ ወስደው የአካባቢውን ማህበረሰብ እና የወረዳውን ምክር ቤት በማስተባበር መሰል ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

በመቀጠልም የወረዳው የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጽ/ቤት የህፃናት መብት ደህንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ አቶ በየነ ደረጃው ለ3 አመታት ለእነዚህ በችግር ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የገቢ ማስገኛ እና ችግራቸውን በዘላቂነት ለመፍታት የሚረዳ የእህል ወፍጮ የፕሮጀክት አፈፃፀምን ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡

በመጨረሻም በወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ማለደ ወደፊት ፕሮጀክቱን በውጤታማነት ለመጠቀምና ለታሰበው አላማ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል የስራ አቅጣጫ ተሰጥቶ እና ድጋፍ ላደረጉ አካላት የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ ወፍጮውን በማስጀመር ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡



