ለእንስሳት ቀዶ-ጥገና ህክምና ባለሙያዎች የክህሎት ማዳበሪያ ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው
በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ለእንስሳት ቀዶ-ጥገና ህክምና ባለሙያዎች የክህሎት ማዳበሪያ ስልጠና ከየካተት 16- 19/ 2012 ዓ.ም እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ስልጠናው እየተሰጠ የሚገኘው በሰሜን፣በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለተሰማሩ 30 ለሚሆኑ የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች ነው፡፡

ከየአካባቢው ከፍተኛ የማህበረሰብ አገልግሎት ጥያቄዎች ቢኖሩም ከዩኒቨርሲቲው አቅም አንጻር እየታየ ለህብረተሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ መሆኑን የእንስሳት ሕክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፀጋው ፈንቴ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው አንስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገ/ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ስልጠናውን በንግግር ሲከፍቱ፣ ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት አንዱ ለባለሙያዎች አጫጭር የሥራ ላይ ስልጠናዎችን በመስጠት በእውቅትና ክህሎት የተሻሉ ሰራተኞችን በመፍጠር ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተለይም የእንስሳት ህክምናና እርባታ ኮሌጅ የኢኮኖሚ አቅም ለሌላቸው እና ለአካል ጉዳተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ በኮሌጁ የተዳቀሉ የተሻሻሉ በርካታ የወተት ጊደሮች እና ወይፈኞችን በተደጋጋሚ በማበርከት እያገዘ መሆኑን ም/ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል፤ አያይዘውም፣ “ስልጠናው የእርስ በርስ መመማሪያ ነውና የአሰራር ልምዳችሁን የምትጋሩበትና የምታዳብሩበት አጋጣሚ ነው፣”ብለዋል፡፡ ፕ/ር መርሻ እንዳሉትም ዩኒቨርሲቲው በምስራቅ አፍሪካ ደረጃውን የጠበቀ የእንስሳት ህክምና ማስተማሪያ ሆስፒታል በመገንባት፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት ላይ በመሆኑ ለሙያው መዳበር መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡

ስልጠናው በሶስት ዙር የሚሰጥ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው ዙር መሆኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ቀዶ-ጥገና ሀኪም ዶ/ር አዲስ መሀመድ ገልጸዋል፡፡ የስልጠናው ትኩረትም የእንስሳት ቀዶ ጥገና ህክምና አሰራር መሰረታዊ ሂደቶችን በተመለከተ ቀዶ ጥገና የሚከናወንበት የአካል ክፍል፣ የማደንዘዣ አሰጣጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተግባራዊ ስልጠና መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



