ለከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ተማሪዎች በተንቀሳቃሽ የሳይንስ ላቦራቶሪ የተግባር ትምህርት ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የኬሚስትሪ፣ የፊዚክስና የባዮሎጂ ት/ት ክፍል መምህራን በአይንባ አጠቃላይ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ የ11ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከየካቲት 26 – 29/2012 ዓ.ም ሲሰጥ የነበረው ተንቀሳቃሽ የሳይንስ ላቦራቶሪ (የሙከራ ማሳያ) የተግባር ትምህርት ተጠናቀቀ፡፡

“የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም እኛ የሳይንስ መምህራን በጎንደርና አካባቢው ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት መሰረት፣ የከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በሙከራ የታገዘ የሳይንስ ትምህርት በበቂ ሁኔታ እንደማያገኙ ለማወቅ በመቻላችን፣ ተንቀሳቃሽ የላቭራቶሪ ትምህርት ለመስጠት አቅደን ተነስተናል፡፡” ያሉት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር በውቀቱ መሀሪ ናቸው፡፡

አስተባባሪው አያይዘውም ሀገራችን ኢትዮጵያ በሳይንስ ዘርፍ ከፍተኛ መሻሻልና እድገት እንድታሳይ ከተፈለገ ኮቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ታዳጊ ተማሪዎችን ከአዳዲስ ቴክኖሎጅዎችና የሳይንስ ትምህርቶች ጋር ማስተዋወቅና ማለማመድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም አሉ ዶ/ር በውቀቱ እነዚህ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገቡ ለተግባር ትምህርት እምብዛም እንዳይቸገሩ ይረዳልም ብለዋል፡፡

በማዕከላዊ፣ በሰሜንና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለሚገኙ የተመረጡ 9 ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት ተማሪዎች በተመሳሳይ ቦታው ድረስ በመሄድ የተሟላ የላቭራቶሪ ቁሳቁሶችንና ቴክኒሻኖችን በመያዝ አገልግሎቱን በቀጣይ ቀናት ለመስጠት አቅደው እየተንቀሳቀሱ እንደሁኑ አስተባባሪው አክለው ገልጸዋል፡፡

የአይምባ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ እሸቱ አሳየ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዋጋ ከት/ት ቤቱ አቅም በላይ የሆኑ የላቦራቶሪ ቁሳቁሶችንና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያላቸውን ምሁራን ቦታው ድረስ በማምጣት፣ የት/ት ቤቱ ተማሪዎች ከዘመናዊ ቴክኖሎጅዎችና አዳዲስ እውቀቶች ጋር በተግባር እንዲለማማዱ በማድረጉ ለዩኒቨርሲቲውና በፕሮጀክቱ ለተሳተፉ መምህራን ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡



