ለግቢ ውበት ሰራተኞች የስራ ላይ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ፅ/ቤት ለዩኒቨርሲቲው የግቢ ውበት ሰራተኞች የዩኒቨርሲቲውን ግቢ ማስዋብና አረንጓዴ ማድረግ ላይ ያተኮረ ስልጠና ከሰኔ 21-23/2013 ዓ/ም ለሶስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና በማራኪ አልሙኒየም ህንፃ ተሰጥቷል፡፡

በዚህ መርሐ ግብር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሰረት ካሴ፣ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታውና የአምስቱም ግቢ የግቢ ውበት ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በርካታ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን እየሰራ ቢሆንም በግቢ ውበት ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውስን መሆናቸውን በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግራቸው ያነሱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በቀጣይ እንደ ዩኒቨርሲቲ ግቢ የማስዋብ ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ ሁሉም ግቢዎች አረንጓዴ፣ ፅዱ፣ የስራ ተነሳሽነትን የሚጨምሩ፣ ለመዝናኛነት የሚያገለግሉና ቱሪስት ሊስቡ በሚችሉ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባም ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ይህንን ለመፈፀም ደግሞ ሰራተኞች የሚሰጠውን ስልጠና ተጠቅመው ሙያቸውን የሚያሻሽሉበት በሌላ መልኩም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአረንጓዴ ልማት እየተደረገ ያለን ርብርብ ትልቅ ኃላፊነት የሚወጡበት እንደሆነ ዶ/ር አስራት አሳስበዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሰረት ካሴ በእለቱ ተገኝተው ስልጠናውን የሚሰጡትን ከሆርቲካልቸርና ከአርክቴክቸር ትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ የቡድን አባላትን አመስግነው የዩኒቨርሲቲውን ግቢ ውብ፣ ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ የፈፃሚ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሚሰጠውንም ስልጠና በአግባቡ በመከታተል ወደፊት የተሻለ ስራ በመስራት የተሻለ የስራ አካባቢ መፍጠር በሚል እሳቤ ተግተው መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ስልጠናው ለተከታታይ ሶስት ቀናት በላንድ ስኬፕ አሰራር መርሆዎች፣ በችግኝ ተከላና የማራባት ስልት፣ በላውን አሰራር ቴክኒኮች፣ የአካባቢ ማስዋብ ስራ በሰራተኛና በተመልካች ከሚፈጥረው መነቃቃት ባለፈ የመስክ መማሪያ ቤተ-ሙከራ አድርጎ መጠቀም በሚያስችል መልኩ እንዴት እንደሚሰራ፣ምን አይነት አትክልቶች እንደሚያስፈልጉ የት ቦታ ሊተከሉ እንደሚችሉና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄና እንክብካቤ በሚሉ ርዕሶች በፅንሰ ሃሳብና በተግባር ትምህርት ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡ስልጠናው በሆርቲካልቸር፣ በደን ሳይንስና በአርክቴክቸር ባሙያዎች ተሰጥቷል፡፡




