ለግዥና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ሠራተኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ሲያካሂዱት የነበረው ስልጠናዊ ግምገማ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት በተለያዮ የሥራ ክፍሎች ላይ የተነሱ ችግሮችን በመለየትና በአጭርና በረጅም ጊዜ በመፍታት ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደሚገባ ጠንካራ አቋም ተወስዷል፡፡

ይህን ተከትሎ በሁሉም ግቢዎች ለሚገኙ የግዥና ንብረት አስተዳደር ሠራተኞች በሙሉ ከነሐሴ 26/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መሰጠት ጀምሯል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን ስልጠናውን በንግግር አስጀምረዋል፡፡ የግዥ ሥርዓቱ ተቋማዊና በሀገር አቀፍ ደረጃ ውስብስብና ክፍተት እንዳለበት ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ግን እንደ ተቋም ያሉብንን ችግሮች ለመቅረፍ በአዲሱ የበጀት ዓመት ሁሉም ሰራተኞች እራሳን ለለውጥ በማዘጋጀትና የውስጥ ችግሮችን በመፍታት በየተመደቡበት የሥራ ክፍል የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በአንክሮ አሳሳስበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ወቅቱንና ዘመኑን የዋጀ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ለሁሉም የስራ ክፍሎች ለመስጠት አቅጣጫ እንዳስቀመጠም ዶ/ር አሥራት ተናግረዋል፡፡ የተቋሙ ሠራተኞች እውቀትና ክህሎት ተኮር ስልጠናዎችን ከመውሰድ በተጨማሪ በቅንነትና በታማኝነት ተቋሙን ብሎም አገርን ማገልገል እንዳለባቸው ጠንከር ያለ አመራርም ሰጥተዋል፡፡



