
ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳት ጥናትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በ2013 ዓ/ም አዲስ ገቢ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን በመቀበል ‹‹አካል ጉዳተኞችን አካታች፣ ምቹና ዘላቂ የተሻለ ዓለምን በድህረ ኮቪድ 19 እንገንባ» በሚል መሪ ቃል የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ሰኔ 28/2013ዓም በማራኪ ግቢ አልሙኒዬም ህንፃ አዳራሽ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡

በፕሮግራሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳት ጥናትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አስቴር አስራት፣ የጋራ ኮርሶች ማስተባበሪያ ዲን ዶ/ር ካሳሁን ጋሹ ፣ በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ረዳት ሬጅስትራር ኃላፊ መ/ር ብስራት ወርቁ፣ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች አስተባባሪ ሲስተር አድና ደምሴ፣ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የተማሪዎች ካውንስል ፕሬዚዳንት ተማሪ ዝናሽ ዘውድዬ፣ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና በማስተርስ ካርድ ፋውንዴሽን ወደ ዩኒቨርሲቲው የተመደቡ አዲስ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ፕሮግራሙ ተካሂዷል፡፡
በዚህ መርሐ ግብር የአካል ጉዳት ጥናትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አስቴር አስራት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በንግግራቸውም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በምዝገባ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን እስቀድሞ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ ተማሪዎች የሚጠበቅባቸው ነገር ምን እንደሆነ፣ በስርአተ ትምህርቱ የጋራ ኮርሶችና የዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳት ጥናትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ ስለሚሰጣቸው ድጋፎች ግንዛቤ ለመፍጠር አላማ ያደረገ ፕሮግራም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በመቀጠል የጋራ ኮርሶች ማስተባበሪያ ዲን በሆኑት በዶ/ር ካሳሁን ጋሹ አማካኝነት የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ስለሚወስዷቸው የጋራ ኮርሶችና በአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን በተመለከተ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ አድርገዋል፡፡ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ሊተገብሯቸው ስለሚገቡ ህጎችና ደንቦች ግንዛቤ በመፍጠር መብትና ግዴታቸውን አውቀው ተግባራዊ በማድረግ የተሳካ የትምህርት ጊዜ እንዲኖራቸው ለማድረግ አላማ ያደረገ ገለፃም በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ረዳት ሬጅስትራር ኃላፊ በመ/ር ብስራት ወርቁ ቀርቧል፡፡ በዶ/ር አስቴር አስራት በኩል ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳት ጥናትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ ስለሚሰጣቸው ድጋፎች ምንነት፣ መቼ እንደሚሰጡ፣ እንዴት እንደሚሰጡና ከተማሪዎች ምን እንደሚጠበቅ ሰፊ ማብራሪያ ሰጠዋል፡፡


በመጨረሻም የተለያዩ የስነ-ጽሁፍ ስራዎች ቀርበው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡