ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠ/ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ድጋፍ ተደረገ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚያከናውናቸው በትምህርት፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጅ ስራዎችና በመሳሰሉ ተግባራት ፕሮጀክቶችን ነድፈው በአጋርነት የሚሰሩ በርካታ የሀገር ውስጥና የሀገር ውጪ ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዳሉ ሁሉ፣ በተቋሙ የሚሰሩ ተጨባጭ ስራዎችን በውል በመገንዘብ ለዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርጉ ድርጅቶችና ግለሰቦችም ቀላል የማይባሉ ናቸው፡፡
ለዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን መካከል ነዋሪነታቸው በሀገረ አሜሪካ – ዋሽንግተን ዲሲ የሆኑ የህክምና ባለሙያ ሲ/ር ማርታ ገ/ስላሴ አንዷ ናቸው፡፡ ሲ/ር ማርታ በአሜሪካን ሀገር በስራ ላይ የሚገኙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቀድሞ ተማሪዎችን/ምሩቃንን (Alumni) በማስተባበር ለጤናው ዘርፍ የሚያግዙ አያሌ ድጋፎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ለአብነት ያክል የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዙ የህክምና ቁሳቁሶች (ከ 80 ካርቶን በላይ) ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ሲ/ር ማርታ በተመሳሳይ አሜርካን ሀገር የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማማከርና በማስተባበር 60 ዊልቸሮች (መንቀሳቀሻ ወንበሮች)፣ 39 ክራች (የመደገፊያ በትሮች) እና 10 ወከር (መራመጃ) ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ (በም/ፕሬዚዳንት ማዕረግ) ለዶ/ር አሸናፊ ታዘበው ዛሬ ታህሳስ 7/2013 ዓ.ም አስረክበዋል፡፡
ሲ/ር ማርታ የህክምና ቁሳቁሶቹን ሲያስረክቡ፣ “ሀገራችን በጤናው መስክ የሚያስፈልጋትን ቁሳቁሶች የመግዛትም ሆነ የማምረት ውስንነት ስላለባት እኛ ትውልደ ኢትዮጵያውን ተባብረን ይህንንን ችግር በፈቃደኝነት ልንፈታ ተነሳስተናል፤ ሆኖም ግን ከግምሩክ ባለስልጣን ጋር በተያያዘ ቀላልና ፈጣን አሰራሮች እንዲኖሩ ቢደረግ ደግሞ ከዚህ በተሻለ ፍጥነትና አቅርቦት የወጣንበትን ማህበረሰብ ለማገዝ ቁርጠኝነቱ አለን፣” ብለዋል፡፡
ዶ/ር አሸናፊ በበኩላቸው በድጋፍ መልኩ የተበረከቱት የህክምና ቁሳቁሶች ወቅቱን የጠበቁና የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉን አሁናው ችግር ከግምት ውስጥ ያስገቡ በመሆናቸው ምክንያት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር አሸናፊ አያይዘውም ቁሳቁሶቹን ለተገቢው ዓላማ በሚገባ እንዲውሉ እናደርጋለን ብለዋል፤ ለዚህ ሰናይ ተግባር ለተሳተፉ የቀድሞ የኮሌጁ ተማሪዎችና አጋር አካላትም ልባዊ ምስጋና አቅርበውላቸዋል፡፡
እኛም “ካለው ላይ አካፍሎ የጎደለው የለም!” እያልን ለዩኒቨርሲቲ ሆስፒታላችን ለተደረገው ድጋፍ አጋርነታችሁን ለሳያችሁን ሁሉ በያላቸሁበት የላቀ ምስጋናችንን እናቀርባለን! በርቱ ተበታሩ እንላለን!
**************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 7/2013 ዓ.ም







