ለ2ኛ ደረጃ መምህራን የሥነ-ማስተማር ዘዴ ክህሎት ማበልፀጊያ ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ትምህርት ኮሌጅ ለ2ኛ ደረጃ መምህራን የሥነ-ማስተማር ዘዴ ክህሎት ማበልፀጊያ ስልጠና በማክሰኝት ከተማ ሰጠ ፡፡

ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የሥነ-ትምህርት ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ክንዴ አበጀ እንደገለፁት ይህ ስልጠና መምህራን የነበራቸውን የስነ-ማስተማር ዘዴ የማስታወስና ክህሎትን የማበልፀግ ተግባርን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል ፡፡የማስተማር ዘዴ ከጊዜና ከቴክኖሎጅ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ መምህራን በየጊዜው አጫጭር ስልጠናዎችን ቢያገኙ ክህሎታቸውን ከማዳበራቸው በተጨማሪ ተማሪውንና የትምህርት ስርዓቱን የሚጠቅም ተግባር እንዲያከናውኑ ይረዳል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊ የሆኑት የማክሰኝት 2ኛ ደረጃ ርዕሰ-መምህር አቶ አገኘሁ ጋሹ በበኩላቸው ሥልጠናው የመማር ማስተማር ዘዴውን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ቢሰራ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚችል የተረዳንበትና ከልማዳዊ አሰራር እንድንወጣ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የአቡነ-ሰምራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት በላይነሽ ጌታሁን ስልጠናው በመማር ማስተማር ስነ-ዘዴው ላይ የተለያዬ ሀሳብ ለሚኖረን መምህራን ጥሩ የክህሎት ማበልፀጊያ ነው፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይህን ስልጠና ከቻለ ለሁሉም መምህራን የሚዳረስበትን መንገድ ቢያመቻች በመማር ማስተማሩ ላይ መልካም ስራ መስራት ይቻላል በማለት አስረድተዋል፡፡ ስልጠናው ከመጋቢት 24 እስከ መጋቢት 26/2013 ዓ.ም. ተሰጥቷል፡፡




