ላሞችን ለወሊድ ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያስችል የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚከናወኑ የማህበረሰብ አገልግሎቶች ይበልጥ ተጠናክረው እየቀጠሉ ይገኛሉ፡፡ ስልሆነም የኮሌጁ መምህራንና ተመራማሪዎች በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለሚገኙ አርብቶ አደሮች (በላም እርባታ ለተሰማሩ ግለሰቦች) በሆርሞን (PGF2 alpha) አማካኝነት በተገደበ ጊዜ ብዛት ያላቸው ላሞችን ለወሊድ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ (ሽል ማሞቅ/ማድራት) ላይ ትኩረት ያደረገ ተግባር ተኮር የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መጋቢት 29 እና 30/2013ዓ/ም ተሰጠ ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሽመልስ ዳኛቸው ስልጠናውን በንግግር ከፍተዋል፡፡ ኮሌጁ የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር በመቀየር አያሌ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችንና የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር ሽመልስ ተናግረዋል፡፡ መሰል ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም በንግግራቸው ገልጸዋል፡፡

በላም እርባታ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ላሞችን ወደ ድራት የማምጣት ቴክኖሎጅ ላይ ክፍተት እንደነበረባቸው በጥናት በመረጋገጡ ምክንያት ስልጠናው እንዳስፈለገ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡




