“መቅደላ 150” ኮንፈረንስ እና ኢግዚበሽን ዝግጅት
ኢትዮጵያ ታሪኳን፣ ነፃነቷን፣ ጥበቧን፣ ባህሏን፣ ወጓን እና ቅርሷን ለመጠበቅና ለባዕዳን ላለማስደፈር ሲሉ ብዙ ጀግኖች ወድቀዋል፤ ህይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ለዚህ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ታሪካዊው የሚሊኒየሙ ጀግና መይሳው ካሳ ሃይሉ (አፄ ቴዎድሮስ) ናቸው፡፡ ስለሀገራቸው አንድነት እና እድገት ሲሉ ለተሰውት አፄ ቴዎድሮስ ባለ ቅኔዎች ተቀኙላቸው፤ ዜመኞች አዜሙላቸው፤ ፎካሪዎች ፎከሩላቸው፤ ገጣሚዎች ገጠሙላቸው፤ ደራሲዎች ደረሱላቸው፤ ሰዓሊዎች በቀለማቸው አነሷቸው፤ትውልዱ ለዘመናት ለትውልድ ትውልድ ስራቸውን፤ጀግንነታቸውንና ስማቸንው ሲዘክር ኑሯል፤ አሁንም ይዘክራል፡፡ እንደዛሬው መንገድ ሳይኖር፣ ጫካውንና ዱሩን ጥሰው፣ ተራራውን ወጥተው፣ ገደል ሸለቆውን ወርደው፣ የወንዝ ሙላቱን ዋኝተው ተሻግረው፣ ቁርና ሀሩሩን ታግሰው ከአገር አገር ዞረው፣ ተንከራተው ተረበው፣ ተጠምተው፣ በእሾህና ጋሬጣ ተወግተው የአንዲት ኢትዮጵያ አንድነትን መሰረት ጥለው ከላፉ እነሆ 150 አመታትን ሊያስቆጥሩ አምስት ወራት ብቻ ይቀራሉ፡፡
[widgetkit id=7783]
ህይወታቸውን ለታሪካዊቷ ሀገራቸው አሳልፈው ለሰጡት ቆራጡ ጀግና አፄ ቴዎድሮስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ “መቅደላ 150” በሚል ስያሜ በኮንፈረንስ እና በኢግዚበሽን በአገር ደረጃ መታሰቢያውን ለመዘከር የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ቅድመ ዝግጀት በማድረግ ላይ ነው፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ የሚመራውና የሶሻል ሳይንስ እና ሂውማኒቲስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ካሳሁን ተገኝ ሰብሳቢነት የሚካሄድ ዘጠኝ የተለያዩ ኮሚቴዎች የተዋቀረ ሲሆን፤ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህራን በተለያዩ ቡድኖች በመደራጀትና ስራዎችን በመከፋፈል የመይሳው ካሳን ታሪክ ትክክለኛ በሆነ መልኩ ለመክተብ የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብ ላይ ናቸው፡፡
ከዚህ መረጃዎችን በማሰባሰብ ላይ ካሉት ቡድኖቸ መካከል የመጀመሪያው ቡድን አራት አባላትን የያዘ ሲሆን፤ አባላቱ የንጉሱን የትውልድ ቦታ፣ ፊደል የቆጠሩበትን እና የተማሩበትን የኃይማኖት ተቋም፣ አጽማቸው በክብር ያረፈበትን እና አሁንም የሚገኝበትን ገዳም፣ የሸፈቱበትን ጫካና ዘመዶቻቸው የሚኖሩበትን አካበቢ አይቶ እና መረጃ ሰብስቦ በሰላም ወደ ሰላሙ ዩኒቨርሲቲ ተመልሷል፡፡
የጥናት ቡድኑ ታሪካዊውን የማህበረ ስላሴ አንድነት ገዳም (ዳሩ ሳት ማህሉ ገነት በመባል የሚታወቀውን ገዳም)፣ በእግር አራት ሰዓት እንዲሁም ያለጫማ አርባ ደቂቃ ያህል የሚያስጉዘውን 1350 ሜትር ከፍታ ያለውን የማህበረ ስላሴን ተራራ ወጥተው፣ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርሰውን ሙቀት ተቋቁመው የጀግናውን የመቃብር ስፍራ ጎብኝተው፣ ለነብሳቸው ብቻ የሚኖሩትን የገዳሙን መነኮሳት አግኝተው ንጉሱ ፊደል የቆጠሩበትን እና ዳዊት የደገሙበትን እንዲሁም አጽማቸው በከብር ያረፈበትን ስለ መይሳው አሉ የሚባሉትን መረጃዎች ጠይቀው እንዲሁም የተማሩበትን “መምህር አምባ” በመባል የሚጠራውን ተራራ አይቶና ጎብኝቶ ተመልሷል፡፡ በአጠቃላይ ቡድኑ ከህዳር 16/2010 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት በገንደ ውሃ፣ በመተማ፣ መሽንፋ፣ በገለጎ፣ በቴዎድሮስ ከተማ፣ በማህበረ ስላሴ ገዳም የነበረው ቆይታ የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በመጨረሻም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር መምህር የሆኑት አቶ ግርማ ታያቸው ባሰተላፉት መልዕክት ዘገባየን ልቋጭ፤ በተለያዩ አቢያተ ክርስቲያንት ያሉ ስለ አፄ ቴዎድሮስ የተጻፉ የብራና ላይ ጽሑፎች ካሉ፣ በግለሰብ ደረጃም እንዚህን መስል የግዕዝ መዛግብት ካሉ በቀጣይ ለሚደረገው ኮንፈረንስ እና እግዚቢሽን መሳካት የላቀ ድርሻ ያለቸው ከመሆኑም በአሻገር ለመጭው ትውልድ ትክክለኛ ታሪክ ሰንዶ ለማቆየትም እጅግ ጠቃሚ ስለሆኑ ትብብራችሁ አይለየን ብለዋል ፡፡ ስለሆነም የሚመለከታቸው ሁሉ መሰል መረጃዎችን ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ በስልክ በ 0581141232 ወይም በአካል ማድረስ ይቻላል ፡፡ “መቅደላ 150” በሚል ስያሜ በኮንፈረንስ እና በኢግዚበሽን በአገር ደረጃ መታሰቢያውን ለመዘከር የሚከናወኑ የተለያዩ ስራዎችን እየተከታተልን እንዘግባለን፡፡
ዘጋቢ፡- ይላቅ አለባቸው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



