መፍትሄ የተሰኘ የባለ አንድ መስመር የጤፍ መዝሪያ ማሽን የቴክኖሎጂ ትውውቅና የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የጤፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያግዝ መፍትሄ የተሰኘ የባለ አንድ መስመር የጤፍ መዝሪያ ማሽን የቴክኖሎጂ ትውውቅና የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ለአርሶ አደሮችና ለባለድርሻ አካላት ሚያዚያ 3/2013ዓ/ም በኮሌጁ መማሪያ ክፍልና በእርሻ ጣቢያው ተግባራዊ ስልጠና ተሰጠ፡፡
ስልጠናው ለምስራቅ ደንቢያ ወረዳ የሰንበት ደብር ቀበሌ እና በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ለሃምስ ፈጅና ለታች ጠዳ ቀበሌዎች ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች የወረዳ የግብርና የሰብል የስራ ሂደት፣ የኤክስቴንሽን፣ የማህበራት ባለሙያዎች በፅንሰ ሃሳብና በተግባር ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

በመርሃ ግብሩ በጤፍ አመራረት ስነ-ዘዴ ላይ ያተኮረ ገለፃ በእፅዋት ሳይንስ መምህሩና በፕሮጀክቱ ረዳት አስተባባሪ በመ/ር ይገረም መንግስት የተሰጠ ሲሆን ፣ ጤፍን በመስመር የመዝራት ጥቅም በሚል በምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መ/ሩ በታዬ መለሰ ተሰጥቷል፡፡ በመቀጠልም በፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ በመ/ር ተገኘ ደርቤ የመፍትሄ የጤፍ መዝሪያ ማሽን አስፈላጊነትና ጥቅም፣ በአርሶ አደሮቹ እንዴት ማግኘትና ማስፋፋት ይቻላል በሚል ርዕስ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከተሰጠው የፅንሰ ሃሳብ ስልጠና የጎንደር ዩኒቨርሲቲን የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ ረ/አስተባባሪ ዶ/ር ውለታው መኩሪያውን ጨምሮ በሌሎቹ የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪና ረ/አስተባባሪዎች አማካኝነት ሰልጣኞች በጠዳ ግቢ የእርሻ ጣቢያ ቴክኖሎጂውን በተግባር እንዲለምዱት ተደርጓል፡፡

ይህ መፍትሄ የተሰኘ የባለ አንድ መስመር የጤፍ መዝሪያ ማሽን ቴክኖሎጂ ከተለመደው የአዘራር ዘዴ ጋር ሲነፃፀር የዘር ብክነትን በሄክታር ከ50% ወደ 10% እንደሚቀንስ፣ በሰብሎች መካከል እኩል እርቀት እንዲኖር እንደሚያደርግ፣ በሰብልና በአረም መካከል ርቀት እንዲኖር እንደሚያስችል፣ በዘር መዝራት ወቅት የሚከሰት የወገብ ህመምን እንደሚቀንስና የጉልበት ብክነትን በአራት እጥፍ ወይም 75% እንደሚቀንስ የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ መ/ር ተገኘ ደርቤ ገልጸዋል፡፡ መ/ር ተገኘ አያይዘውም ቴክኖሎጂው የጤፍ ምርትን በሄክታር ከ14.99 በኩንታል ወደ 24.35 በኩንታል እንዲጨምር እንደሚያደርግና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎቹን አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ስልጠናውን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ አርሶ አደሮቹ በኮሌጁ መምህራንና ተመራማሪዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በተከታታይ እንዲሰጣቸውና ከዘር አቅርቦት ጋር እንዲሁም ሌሎች ጥያዎችን አንስተው ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡



