ማህበራዊ ግብይት ለተሻለ ህይወት በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ማህበራዊ ግብይት ለተሻለ ህይወት በሚል የማህበረሰቡን የደም ልገሳ ባህል ለማሳደግ አላማ ያደረገ ስልጠና በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ማሰልጠኛ ክፍል ግንቦት 19 እና 20/2013 ዓ/ም ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናው በትምህርት ክፍሉ መምህራን የተሰጠ ሲሆን፣ ወቅታዊ የደም ልገሳ አቅርቦትና ልገሳ፣ የአቅርቦትና ፍላጎት ሁኔታ በሀገራችንና በአማራ ክልል፣ የማህበራዊ ግብይት ምንነት፣ ማህበራዊ ግብይትና ደም ልገሳ፣ ከደም ልገሳ ጋር የተያያዙ ሙያዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ርሶች ዙሪያ ያተኮረ ሲሆን ደም ከመለገስ ጋር የተያያዙ እና የተዛቡ አመለካከቶች፣ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች ላይም ውይይት ተካሂዷል፡፡

በመጨረሻም የማህበረሰቡን የደም ልገሳ ባህል ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ከመንግስት መስሪያቤቶች፣ ከዩኒቨርሲቲውና ከማህበረሰቡ ምን ይጠበቃል በሚል ሰፊ ውይይት ተካሂዶ የወደፊት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡ ከዚህ ቀደም መሰል ስልጠና ለጎንደር ከተማ እና ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት መሰጠቱ ይታወሳል፡፡



