ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በማህበረሰብ አቀፍ መልሶ መቋቋም ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲና ከኪዊንስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በማህበረሰብ አቀፍ መልሶ መቋቋም/Community Based Rehabilitation/ በሰርቲፊኬት ደረጃ ያሰለጠናቸውን የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎች የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስ/ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው እና ዩዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራር ኃላፊ ዶ/ር ግዛቸው ሙሉጌታን ጨምሮ የተለያዩ የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስ/ሆስፒታሉ፣ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽንና ሲ.ቢ.አር ፕሮግራም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሚያዚያ 9/2013 ዓ.ም አስመረቀ፡፡

በህብረተሰቡ ውስጥ ከአካል ጉዳተኞች ጋር የተያያዙ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በመቅረፍ በኩል ትልቅ ስራ የመስራት ኃላፊነት እንዳለባቸው በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ዋና አካዳሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ ለተመራቂዎቹ አሳስበዋል፡፡ በሲ.ቢ.አር ፕሮግራም ላለፉት 16 አመታት በጎንደርና አካባቢው በርካታ የማህበረሰብ አቀፍ ተሀድሶ ፕሮግራሞችን ሲያካሂድ የቆየው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቀስ በቀስም ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ስራውን በስፋት መቀጠሉን የማስተር ካርድ ፋውንዴሽንና ሲ.ቢ.አር ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን መኮነን ተናግረዋል፡፡ እስከዛሬ በሀገራችን ውስጥ የማህበረሰብ አቀፍ ተሀድሶ ፕሮግራም ትምህርት እንደማይሰጥ የገለጹት ዶ/ር ሰለሞን ፣ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ከኪዊንስ ዩኒቨርሲቲና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የማህበረሰብ አቀፍ መልሶ መቋቋምን እንደ አንድ መደበኛ ትምህርት ለመስጠት ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ በሰርቲፊኬት ደረጃ መሰጠት መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት የጤና አቅጣጫን መሰረት ያደረጉ አምስት የንድፈ ሀሳብ ኮርሶች እና አንድ የተግባር ትምህርት በስልጠናው የሚሰጡ ሲሆን በቀጣይም ስልጠናውን በሰርቲፊኬት ደረጃ በኦንላይን ለመስጠት በመታሰቡ ማንኛውም ሰው በተለያየ ሀገር ሆኖ ባለበት በበይነ መረብ መከታል የሚችል መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፤ በአጠቃላይ 47 ተማሪዎች ስልጠናውን እየወሰዱ ሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በመጀመሪያው ዙር ዘጠኝ ሰልጣኞች ዛሬ ሲመረቁ ቀሪወቹ ደግሞ ኮርሱን ሲያጠናቅቁ እንደሚመረቁም ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም የማህበረሰቡን ፍላጎት ጥናት በመድረግ በአድቫንስድ ዲፕሎማና በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ትምህርቱ ሊሰጥ የሚችልበት እድል ሊኖር እንደሚችል ዶ/ር ሰለሞን መኮነን ጠቁመው፣ ከዳሰሳ ጥናት ጀምሮ ለስርአተ ትምህርቱ አሁን ያለበት ደራጃ መድረስ ጉልህ አስተዋፅኦ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፤ ማስተር ካርድ ፋውንዴስን ከዚህ በፊት 10 ተማሪዎችን በድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ማስመረቁንም አስታውሰዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፊዚዮቴራፒስትና የማስተር ካርድ ፋውንዴሽንና የኪዊንስ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ፋሲካም በበኩላቸው እነዚህ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በተለያዩ የዩኒቨርሲቲው መደበኛ የትምህርት መስኮች በጥር ወቅት የተመረቁ ሲሆን በተጨማሪም ጊዜአቸውን አብቃቅተው በመጠቀም ይህንን ስልጠና ለ8 ሳምታት በመውሰድ ዛሬ መመረቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም የወሰዱት ስልጠና በማህበረሰብ መልሶ መቋቋም የተለያዩ ተግባራትን ለመስራት አቅማቸውን በማጎለበት ትልቅ ግብአት ይሆናቸዋል ብለዋል፡፡ አምስቱንም የንድፈሀሳብ ሞጅዩሎች በኢ-ለርኒንግ ለመስጠት ዝግጀቱ መጠናቀቁን የገለፁት ስራ አስኪያጁ፣ በእቅድ ደረጃ በሚቀጥሉት የተወሰኑ አመታት 175 ያህል የትምህርት እድል ለመስጠት መታሰቡንም ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሙ በፊዚዮቴራፒ ትምህርት ክፍል ስር በመሆኑ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በኋላም በቋሚነት ለመቀጠል መሰረት እንደሚኖረው አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
በስልጠና ቆይታቸው በተለይም በመሰረታዊ የኮምፒዩተር ክህሎት ፣በአካል ጉዳተኞች አካታችነት ህግ ማዕቀፎች፣በስራ ፈጠራ፣ በህይወት ክህሎት ፣በአመራር ጥበብና በገንዘብ አያያዝ ዙሪያ ጥሩ ግንዛቤ እንደተፈጠረላቸው ከተመራቂዎች መካከል ቤተልሄም አሰፋ እና መለሰ በላይ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ስልጠናውን መውሰዳቸው ሌሎች የአካል ጉዳተኞችን በአግባቡ ለመርዳት እንደሚያግዛቸው ገልጸው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡




