(ማስታዎቂያ) ትምህርት ለተቋረጠባቸው ግቢ ተማሪዎች በሙሉ
በዩኒቨርሲቲያችን በአብዛኛዎቹ ግቢዎች መማር ማስተማሩ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መስተጓጎሉ ይታዎሳል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከግቢ ለቀው የወጡ ተማሪዎች እንዳሉም ተገንዝበናል፡፡ በዚህም ምክንያት በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የተፈጠረውን መስተጓጎል ለመፍታት እና በዘላቂነት የዩኒቨርሲቲያችን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ከሚመለከታቸው የፌደራል፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደር እና የአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር እየሰራን የምንገኝ ሲሆን መማር ማስተማሩ በተገቢው ሁኔታ ይቀጥል ዘንድ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በቀን 06/04/2012ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ የሚከተሉትን አንኳር ውሳኔዎች አስተላልፏል፦
1ኛ. ከተለያዮ ውይይቶች ለመረዳት እንደቻልነው የዩኒቨርሲቲያችን መማር ማስተማር የተስተጓጎለበት ዋነኛው ምክንያት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ገበታ ውጭ ሁነው ወደየአካባቢያቸው ተመልሰው የሚገኙ ተማሪዎች መኖራቸው ነው። ስለዚህ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዩኒቨርሲቲያችን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል፤
2ኛ. ትምህርት በተቋረጠባቸው ግቢዎች መማር ማስተማሩ ከረቡዕ ታህሳስ 08/2012ዓ.ም ጀምሮ እንዲቀጥል፤
3ኛ. እስከ ሰኞ ታህሳስ 13/2012ዓ.ም ድረስ በትምህርት ገበታቸው ላይ የማይገኙ ተማሪዎች ቢኖሩ በገዛ ፈቃዳቸው ትምህርታቸውን ያቋረጡ መሆኑ እንዲታዎቅ፤
4ኛ. ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት ከፌዴራልና ከክልል የሚመጡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ከተማሪዎች፤ ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ፣ ከከተማ አስተዳደር እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንዲደረግ፤
5ኛ. ትምህርት እንዲቋረጥና ተማሪዎቻችን ደህንነት እንዳይሰማቸው የሚያደረጉ አካላትን የፌደራልና የክልል የጸጥታ አካላት ተቀናጅተው ከዩኒቨርሲቲው፣ ከከተማ አስተዳደር እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር አጥፊዎችን የመለየትና ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰድ በማድረግ ከመቸውም ግዜ በተሻለ ሁኔታ የተማሪዎቻችን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሰራ፤
6ኛ. የዩኒቨርሲቲው ጸጥታ እንዲታወክ ያደረጉ እና የተለያዩ ጉዳቶችን በማድረስ የተጠረጠሩ ተማሪዎችና ሌሎች አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው እየተከናወነ ሲሆን ጉዳዩ በህግና በማስረጃ ተመስርቶ በፍጥነት እንዲታይና ውጤቱ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲገለፅ በማለት ወስኗል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ



