“ሰላም”ን የተመለከተ ውይይት እየተካሄደ ነው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች ዘንድ የ ‘ሰላሙ ዩኒቨርሲቲ’ የሚል ስያሜ ካገኘ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላት ጋር በጋራ በመስራት ይህንኑ ስያሜ ለማስቀጠል መቻሉን በተለያየ መልኩ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በመሆኑም የዩኒቨርሲው ተማሪዎች የሰላምን ፋይዳ ይበልጥ መረዳት እንዲችሉና እርስ-በእርሳቸው በመከባበርና በመቻቻል ዓለማቸውን አሳክተው እንዲመለሱ ለማስቻል ‘በሰላማዊና ውጤታማ ትምህርት/Peaceful & Purposeful Education እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና አዘል ውይይት በሳይንስ አምባ አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ይህ ውይይት የተዘጋጀው በጎንደር ዩኒሲቨርሲቲና በአሜሪካ ኤምባሲ በጋራ ትብብር ሲሆን፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ደሌሳ ቡልቻ፣ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኝ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ የህዝብ ጉዳይ ስፔሻሊስት/Public Affairs Specialist ብሪታኒ ዲፓሎ፣ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች (1000 የሚሆኑ) በጉባኤው ተሳትፋዋል፡፡

ዶ/ር ካሳሁን ጉባኤውን ሲከፍቱ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲና አሜሪካ ኤምባሲ በበርካታ ጉዳዮች አብረው እየሰሩ እንደሚገኙና ይሄ ግንኙነት ለወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡ ም/ፕሬዚዳንቱ በማያያዝ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጊዜአቸውን በአግባቡ በመተቀም፣ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ትምህርት በመቅሰም፣ የእውቀት አድማስን በማስፋትና ጥልቅ አስተሳሰብን በማዳበር እራሳቸውን፣ ወገናቸውን ብሎም ሀገራቸውን መጥቀም አለባችሁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህንን ዕውን ለማድረግ ማህበራዊ ሚዲያዎችን አወንታዊ በሆነ መልኩ በመጠቀም ሰላምን ማስጠበቅ እንደሚገባ በአንክሮ ተናግረዋል፡፡
ሳይንስና ከፍተኛ ሚንስቴርን በመወከል ዶ/ር ደሌሳ ቡልቻ፣ አማሪካ ኢምባሲን በመወከል ደግሞ ብርታኒ ዲፓሎ የ ‘ሰላም’ን ፋይዳ በተመለከተ ለተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የማነቃቂያ ስልጠናውን እየሰጡ የሚገኙት አቶ ዳዊት ገ/እግዛብሄር ሲሆኑ አቶ ዳዊት በሀገር ውስጥና በሀገር ውጪ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊ ምሁር ናቸው፡፡ ግለሰቡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ራዕያቸውን ለማሳካት መከተል ያለባቸውን ሳይንሳዊ በተለይም በስነ-ልቦና ደረጃ ማጠንከር እሚችሉ መንዶችን ግልጽና ቀላል በማድረግ፣ በማዝናናትና አሳታፊ በሆነ መልኩ በማሰልጠን ላይ መሆናቸውን ለማየት ችለናል፡፡
“እኔ ድንቅ ነኝ! ህልም አለኝ! ህልሜ ዕውን ይሆናል! ህልሜን ለማሳካት ግን ማንኛውንም መስዋዕትነት እከፍላለሁ!” ከስልጠናው ቀንጨብ ተደርጎ የተወሰደ መልዕክት ነው፡፡
ይህ ስልጠና አዘል ውይይት እስከ ነገ የካቲት 22/2012 ቆይታ ይኖረዋል፡፡
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



