ስልታዊ የችግር ትንተናና የአፈታት ሂደትን የተመለከተ ውይይትና ግምገማ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከሚገኙ ሰባት ወረዳዎች የተወጣጡ የጤና ባለሙያዎችንና ኃላፊዎችን ያሳተፈ ስልታዊ የችግር ትንተናና የአፈታት ሂደትን/Strategic Problem Analysis and Solving/ የተመለከተ ውይይትና ግምገማ ሰኔ 19/2013 ዓ.ም በኮሌጁ ድህረ-ምረቃ አዳራሽ ተካሄደ፡፡

ችግሮችን ለመፍታት ከተለምዷዊ አሰራር በመውጣት የተለየ ስልት መጠቀም ያስፈልጋል በማለት ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ዋና አካዳሚክ ዳይሬክተር እና የፕሮጀክቱ ባለቤት ዶ/ር አስማማው አጥናፉ፣ ውይይትና ግምገማ ማካሄዱ በተለያዩ ተቋማት የታየውን የተለያየ የችግር አፈታት ደራጃ ለመዳሰስና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚጠቅም ገልጸው ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና አላማ የጤና ባሙያዎችና አመራሮች በየተቋማቸው ያሉ ችግሮችን በመለየትና ሳይንሳዊ ስልትን በመጠቀም መፍታት እንዲችሉ ማስቻል እንደሆነ የገለጹት በህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ የጤና ስርአትና ፖሊሲ ት/ክፍል መምህር የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር እንዳልካቸው ደሌ፣ ከዚህ በፊት ችግሮችን የመፍታት ስልቶችንና ደረጃዎችን በተመለከተ በአምባ ጊዮርጊስና በማክሰኝት ከተማ ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል፡፡ በዚህም ሰልጣኞች በየተቋማቸው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት በሳይንሳዊ ስልት እንዲፈቱ መግባባት መደረሱን አስታውሰዋል፡፡ ረ/ፕሮፌሰር እንዳልካቸው አያይዘውም ሰልጣኞች በጥናት ሂደታቸው ያደርጉት የነበረውን ሳይንሳዊ የሆነ የችግር ልየታ፣ የችግሮችን ስረ -መሰረት የመለየት ፣ የመፍትሄ አቅጣጫ አቀራረብ እና አተገባበር በተመለከተ የፕሮጀክቱ አስተባባሪወች በየተቋሙ በመንቀሳቀስ የማማከር ተግባር ይሰሩ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

በማማከር ሂደቱም በየተቋሙ የነበሩት የችግር አፈታት ደረጃ የተለያዩ ሆኖ መመልከታቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል፤ስለሆነም ይህ የውይይትና የግምገማ ፕሮግራም መካሄዱ አጥኝዎቹ የደረሱበትን ሁኔታ በማየት፣ አጠቃላይ የነበረውን የአጻጸም ሂደት ለመገምገምና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚረዳም አብራርተዋል፡፡ ችግሮች በየጊዜው መፈጠራቸው የማይቀር ስለሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ይህንን ሳይንሳዊ የሆነ የችግር አፈታት ስልት አሰራር እንዲያስቀጥሉ በዚህ ፕሮግራም መግባባት ላይ መደረሱንም አንስተዋል፡፡



