በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ለወጣቶች ሥልጠና እየተሰጠ ነው
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኬሌጅ የገጠር ልማት ማበልጸጊያና ሥርፀት ትምህርት ክፍል የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ፕሮጀክት ቀርጾ የሥራ ዕድል ፈጠራ ማሻሻያ ስልቶች በሚል ከመጋቢት 30- ሚያዝያ 3/2013 ዓ/ም ድረስ የሚቆይ ሥልጠና በጣቁሳ ወረዳ ለወጣቶች በመስጠት ላይ ይገኛል።

ዋና ዓለማውም የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማሻሻል የተለያዩ ስልቶችን በሥልጠና ለማዳበር የተዘጋጀ ወርክሾፕ ነው።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የገጠር ልማት ማበልጸጊያና ሥርጸት ትምህርት ክፍል መምህር፣ተመራማሪና የኮሌጁ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ በየነ ደርሶ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ የጣቁሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል ሱሌይማን ወርክሾፑን በንግግር አስጀምረዋል።

በመቀጠልም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ሬጅስትራር እና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ደግሰው መላክ “የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ማሻሻያ ስልቶች” በሚል የመጀመሪያውን ጽሑፍ አቅርበዋል።

በቀጣዩ ቀናትም “የቢዝነስ አዘገጃጀትን” አስመልክቶ በአቶ በየነ ደርሶ እንደሚቀርብ የተገለጸ ሲሆን በግብርና ልማት ማበልጸጊያና ሥርጸት ትምህርት ክፍል መምህር፣ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አባል አቶ ተገኘ ደርቤ በበኩላቸው ሥልጠናው በስኬት እንዲጠናቀቅ የማስተባበር ሥራ በመስራት ላይ ናቸው።



