በስራ ፈጠራና በሀብት አያያዝ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ጋራ በመተባበር ከምዕራብ በለሳ፣ ከምስራቅ በለሳ፣ ከእንፍራንዝና ከጣቁሳ ወረዳዎች ለተገኙ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እና የተደራጁ ወጣቶች ከመጋቢት 4-6/2012 ዓ/ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት በማ/ጎንደር ዞን መሰብሰቢያ አዳራሽ በስራ ፈጠራና በሀብት አያያዝ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ፡፡

በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንትርፕራይዝ ልማት መምሪያ ም/ኃላፊ አቶ ዳዊት አቡ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው መኩሪያው፣ የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታው፣ የዞኑ የስራ ፈላጊዎች የግንዛቤ ፈጠራ ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ ገ/መድህን እና ጥሪ የተደረገላቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ስልጠናውን አስመልክተው ቁልፍ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በንግግራቸው ሰልጣኞች በአካባቢያቸው የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው፣ በተለያየ መንገድ ያፈሩትን ገንዘብ በጥንቃቄ በመያዝና በመጠቀም በሚያገኙትም ገንዘብ ራሳቸውን መለወጥ እንደሚገባቸው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው የተሻለ የገንዘብ አያያዝ ግንዛቤ እንደሚፈጥርላቸውና ወደፊትም የዩኒቨርሲቲው ክትትልና ድጋፍ እንደማይለያቸው ገልፀዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንትርፕራይዝ ልማት መምሪያ ም/ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳዊት አቡ፣ በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዘርፉን ልማት ለመደገፍ ምሩቃን ስራ ፈላጊዎች የስራ ፈጣሪነት አስተሳሰባቸውን ከፍ ለማድረግ ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ በእንጉዳይ ምርት የተመረጡ ምሩቃንን በማሰልጠን፣ የዘርፉን ባለሙያዎች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ በማሰልጠንና በተለያየ መንገድ ተከታታይ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አውስተው ለዩኒቨርሲቲው ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል፡፡

በመቀጠልም በመሰረታዊ የስራ ፈጠራ፣ በስራ ፈጠራ፣ በግብይትና በደንበኛ አያያዝ፣ በቢዝነስ እቅድ፣ በሀብት አያያዝና በወጪና ገቢ ዙሪያ በዶ/ር ማረልኝ አዱኛ እና በአቶ ኡመር ሙሀመድ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ የተሰጠውን ስልጠና መነሻ በማድረግም ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



