
በስነ-ምግብ( Nutrition) የዶክትሬት ዲግሪ ስርዓተ-ትምህርት ለመክፈት የውጭ ግምገማ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ የስነ-ምግብ ትምህርት ክፍል በስነ-ምግብ (Nutrition) የዶክትሬት ዲግሪ ስርአተ- ትምህርት ለመክፈት የውጭ ገምጋሚዎችን ያሳተፈ አውደጥናት ሰኔ 30/2013 ዓ.ም በኮሌጁ ምንትዋብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ፡፡

በአውደጥናቱ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ምሁራን በተጨማሪ የተለያዩ የመስኩ ምሁራን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በበይነ-መረብ በመሳተፍ ያላቸውን ሙያዊና ሳይንሳዊ ሀሳብ አጋርተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ኃይልና በትምህርት ፕሮግራሞች እየሰፋ መምጣቱን በመክፈቻ ንግግራቸው የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ ብቁ ምሁራን እንዲኖረን በስታንዳርዱ መሰረት ጥራቱን የጠበቀ የፒ ኤች ዲ ስርአተ ትምህርት እና ምርምር ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል፤ የዩኒቨርሲቲው የወደፊት አቅጣጫም ጥራት ያለው ትምህርትን ችግር ፈች ከሆነ የምርምር ስራ ጋር ማቀናጀት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳሁን አለሙ በበኩላቸው በሀገራችን ያሉ የጤና ችግሮች በብዛት ከአመጋገብ ጋር እንደሚያያዙ አንስተዋል ፤ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ ደግሞ በሳይንስና በምርምር ብቁ የሆኑ የጤና ስርአትን መምራት የሚችሉ ምሁራን ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ ጤናማ ትውልድ የሚገነባው በጤናማ አመጋብ ነው፡፡ስለሆነም በዩኒቨርሲቲያችን በስነ ምግብ/ Nutrition / የሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም መሰጠቱ ከምግብና ከአመጋጋብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በምርምር ለመፍታት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አክለው የገለጹት ዶ/ር ካሳሁን አለሙ ይህ አውደጥናት መካሄዱ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገኙ የመስኩ ምሁራን /ኤክስፐርቶች/ አስፈላጊ እና ገንቢ ምክረ-ሀሳቦችን ለማካተት ታስቦ መሆኑንም ተናግረዋል፤አያይዘውም በስርዓተ-ትምህርቱ ዝግጅትና ግምገማ ሂደት የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ያሳተፈ የውስጥ የስርአተ ትምህርት ግምገማ ከዚህ በፊት መካሄዱ ይታወሳል፡፡