በስነ ምግብ(NUTRITION) የዶክትሬት ዲግሪ ስርአተ ትምህርት ለመክፈት የውስጥ ግምገማ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ የስነ-ምግብ ትምህርት ክፍል በስነ ምግብ (NUTRITION) የዶክትሬት ዲግሪ ስርአተ ትምህርት ለመክፈት የተለያዩ የትምህርት ክፍል ሀላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች እንዲሁም የግቢው የፒ. ኤች .ዲ ተማሪዎችና መምህራን በተገኙበት ሰኔ 10/2013 ዓ.ም በሳይንስ አምባ ፒ ኤች ዲ መሰብሰቢያ አዳራሽ የውስጥ ግምገማ ተካሄደ፡፡

ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ በዚህ አመት አስር የሚሆኑ ተማሪዎችን በፒ. ኤች .ዲ ፕሮግራም ማስመረቁን ያስታወሱት የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ አካዳሚክ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ፣ በዩኒቨርሲቲው በስነ ምግብ (NUTRITION) የዶክትሬት ፕሮግራም ለመክፈት በከፍተኛ ደረጃ የተሟላ ቤተ-ሙከራ ያስፈልጋል፤ ስለሆነም ይህንን ለማሟላት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

የግምገማው ዋና አላማም በሃገራችን ያለውን የስነ-ምግብ ችግር ሊፈታ የሚችል ሰው ሀብት ማፍራት እና የወጣውን ፖሊሲ ሊፈፅም የሚችል አስፈጻሚና ጥንካሬውን እንዲሁም ድክመቱን እየገመገመ ሊያስቀጥል የሚችል የተማረ የሰው ሀይል ማፍራት እንደሆነ የስነ ምግብ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አይሸሽም ካሳሁን ገልፀዋል፡፡




