በስነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል መምህራንና የጤና ባለሙያዎች ለአዕምሮ ህሙማን የበጎ ፈቃድ የአዕምሮ ህክምና እርዳታ ተደረገ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የስነ-አእምሮ ትምህርት ክፍል መምህራንና የጤና ባለሙያዎች በጯሂት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የአዕምሮ ህሙማንና አረጋውያን ምንዱባን ማህበር ውስጥ ለሚገኙ የጤና መድህን ለተሟላላቸው 35 የአእምሮ ህሙማን መጋቢት 18/2013ዓ/ም ከቦታው ድረስ በመገኘት የበጎ ፈቃድ የአዕምሮ ህክምና እርዳታ አድርገዋል፡፡

ይህ የመጀመሪያ ዙር የበጎ ፈቃድ የአእምሮ ህክምና እርዳታ ዘመቻ በጯሂትና በዙሪያው ለሚኖሩ የአዕምሮ ህሙማን በሚኖሩበት አካባቢ ድረስ በመገኘት ህክምና ለመስጠት የታሰበ እንደሆነና እንደመጀመሪያ ለማህበሩ ህሙማን ህክምናው የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ መ/ር ጎሹ ኔንቆ ጨምሮ በረ/ፕሮፌሰር ታደለ አማረ፣ ፣ በክሊኒካል ሳይኮሎጂስትና መ/ር ብዙነህ ተስፋዬ፣ በረ/ፕሮፌሰር ሀረገወይን ሙላት፣በመ/ር ሰላም ቆዬ፣ በአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች በሙላለም ቀለቤና በአስናቀው ወርቁ መሰጠቱን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ በሆስፒታሉ ያለውን ታካሚ እጅግ ብዙ በመሆኑ እንደነዚህ አይነት ህመማንን በበጎ ፈቃድ አቅፎ የሚይዝ ሲገኝ በቦታው ተገኝቶ ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ ትልቅ የአዕምሮ እርካታን የሚሰጥ መሆኑን መ/ር ጎሹ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ወደፊትም በተከታታይ በሚሰሩ የበጎ ፈቃድ ህክምና ስራ ማንኛውም ባለሙያ አብሯቸው ቢሰራ የሚፈቱ በርካታ ችግሮች ስለሚኖሩ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንዲሳተፍ በቡድኑ አባላት ጥሪ ቀርቧል፡፡

የጯሂት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የአዕምሮ ህሙማንና አረጋውያን ምንዱባን ማህበር ከ190 በላይ የሚሆኑ አረጋውያን፣ የአእምሮ ህሙማን፣ ህፃናትና አካል ጉዳተኞችን አቅፎ የያዘ ማህበር እንደሆነ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ብርሀን መልካሙ ያነሱ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለማህበሩ ከአሁን በፊት በምግብ እህል፣ በአልባሳት፣ በንፅህና መጠበቂያና ከዩኒቨረሲቲው ማህበረሰብ የተሰበሰበ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግላቸው እንደቆየ አውስተዋል፡፡ በእለቱ ከፍተኛ የሆነ አርአያነት ያለው ስራ በበጎ አድራጊ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች ህክምና በመሰጠቱ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡
ወደፊትም የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንዲቀጥል፣ የወረዳው አስተዳደር የጤና መድህን ላልወጣላቸው እንዲወጣላቸው ቢያደርግ፣ ሌሎች ባለሙያዎችም በሀሳብ በጉልበት፣ በገንዘብና በሙያቸው እንዲደግፏቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡



