በቢሮ ማሽኖች የጥገና ሥልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የቢሮ ማሽኖች የጥገና ሥልጠና ጥቅምት 13 እና 14 /2013 ዓ.ም በቴክኖሎጅ ኢንስትቲዩት ወርክሾፕ ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ የተሰጠውን ሥልጠና በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት በሃገራችን ኢትዮጵያ ብሎም በዩኒቨርሲቲያችን ለበርካታ ዓመታት በትንንሽ በልሽቶች ምክንያት የተጠራቀሙና ያለ አግባብ ቦታዎችን እያጨናነቁ የሚገኙ የቢሮ ቁሳቁሶችና ማሽኖች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህንንም ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የጥገና ሥልጠናዎች በሙያው የዳበረ ልምድ ባላቸው ሰዎች በተከታታይ መሰጠት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡የቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ውለታው መኩሪያ እንደገለጹት መጠገን የሚችሉ ነግር ግን ሥልጠና ባለመኖሩ በየቦታው ተከማችተው የሚገኙ ንብረቶች የሃገሪቱን ሃብት በአግባቡ እንዳንጠቀም አድርጎን ቆይቷል ብለዋል፡፡ሥልጠናው የተሰጠው አይ.ቲ.ኤስ.ሲ ከተሰኘ ካምፓኒ ጋር በመተባበር ሲሆን አቶ እያሱ ጌታቸው ካምፓኒውን ወክለው እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ለበርካታ የመንግስትና የግል ድርጅቶት እንዲሁም መ/ቤቶች ተከታታይነት ያለውና ውጤታማ ሥልጠናዎችን መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡
በስልጠናው የተካፈሉት ባለሙያዎችም ከባዮ ሜዲካል፣ ከመካኒካል፣ ከኤሌክትሪካል ኢንጅሪኢንግ የትምህርት ክፍሎች ፤ የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ መምህራንና የአይሲቲ ባለሙያዎች ናቸው፡፡በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ሰልጣኞች እንደተናገሩት ተመሳሳይና ረዘም ላለ ጊዜ የሚሰጡ ሥልጠናዎች በተለይም ደግሞ ለይሲቲ ባለሙያዎች እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ አቶ እያሱ ጌታቸው እና የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ አክለው እንደተናገሩት ባለሙያዎቹ ብቁ እስከሚሆኑ ድረስ ሥልጠው የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ሀገራችን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
********************************************************
ህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ጥቅምት 15/2013





