በቢዝናስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ት/ት ክፍል የ2ኛ እና የ3ኛ ዓመት የመደበኛ ቅድመ ምረቃ ተማሪዎች አፄ ፋሲል 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የድጋፍ መስጫ ማዕከል ድጋፍ አደረጉ፡፡
ተማሪዎቹ ሚያዚያ 07/2013 ዓ.ም በአዘዞ ክፍለ ከተማ በአፄ ፋሲል 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ባደረጉት ትምህርታዊ ጉብኝት በትምህርት ቤቱ ለሚገኘው የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የድጋፍ መስጫ ማዕከል ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የድጋፍ ማዕከሉ ማየትና መስማት የተሳናቸው እንዲሁም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ተማሪዎች የሚማሩበት ነው፡፡

በዚህ ድጋፍ ከ100 በላይ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ገንዘብ ከኪሳቸው በማዋጣት የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ሳሙና፣ ሶፍት፣ ሞዴስና ብዛት ያለው ወረቀት ለማዕከሉ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የድጋፍ መስጫ ማዕከሉ አስተባባሪና መ/ርት ፀሀይነሽ መከተ ለማዕከሉ የተደረገውን ድጋፍ አመስግነው ተማሪዎች በትምህርታዊ ጉብኝታቸው የማዕከሉን ችግር በመረዳት መደገፋቸው ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎች ትምህርት ክፍሎችም በተመሳሳይ ተግባር እንዲሳተፉ መክረዋል፡፡
በዕለቱ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ አስቻለው አዳነ (ረዳት ፕሮፌሰር) እና የኮሌጁ የማ/ህ/አ/አስተባባሪ ዶ/ር ዋሴ ጌታሁን የተገኙ ሲሆን በመርሀ ግብሩ መደሰታቸውን ገልፀው መምህሩን እና ተማሪዎቹን አመስግነዋል፡፡
የት/ት ክፍሉ መምህር እና የጉብኝቱ አስተባባሪ አቶ ጌታነህ ዘላለም (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደገለፁት ተማሪዎችን ለት/ት አይነት (ማህበራዊ ግብይት/ Social Marketing) ማሟያ ይሆን ዘንድ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ይዘዋቸው እንደሚሄዱ እና ይህም ተማሪዎች የተለያዩ የማህበረሰብ ችግሮችን እንዲያውቁ እና በተማሩበት መስክ የመፍትሄ ሀሳቦችን እንዲያመነጩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡




