በተንቀሳቃሽ የሳይንስ ላቦራቶሪ ትምህርት መሰጠቱ ቀጥሏል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የኬሚስትሪ፣ የፊዚክስና የባዮሎጂ ት/ት ክፍል መምህራን በወቅን አጠቃላይ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ የ11ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከመጋቢት 01 – 02/2012 ተንቀሳቃሽ የሳይንስ ላቦራቶሪ (የሙከራ ማሳያ) የተግባር ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ለአይንባ አጠቃላይ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃና የመሰናዶ ተማሪዎች ከየካቲት 26 – 29/2012 ዓ.ም ተመሳሳይ የተግባር ትምህርት መሰጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

በጎንደርና አካባቢው የሚገኙ የመሰናዶ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ዝግጅት ላይ ያሉ ተማሪዎች ከአዳዲስ ቴክኖሎጅዎችና የሳይንስ ትምህርቶች ጋር በተግባር እንዲተዋወቁና እንዲማሩ ማድረግ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ መሆኑን አስተባባሪው ዶ/ር በውቀቱ መሀሪ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨረሲቲው የሳይንስ መምህራን ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ብቻ የሚያውቋቸውን ሳይንሶች በተግባር ለማሳየት ቦታው በመገኘታቸው፣ እውቀታቸውንና ልምዳቸውን በማካፈላቸው በወቅን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በአቶ አትርሳው ክንዴ በኩል ልባዊ ምስጋና ቀርቦላቸዋል፡፡ ለሙከራ ማሳያ ምቹ ያልሆኑ መማሪያ ክፍሎችን በማመቻቸትና ተማሪዎቻቻውን ማስተማር በመቻላቸው ርዕሰ መምህሩ ተጨማሪ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሳይንስ መምህራኑ የተሟላ የላቭራቶሪ ቁሳቁሶችንና ቴክኒሻኖችን በመያዝ በማዕከላዊ፣ በሰሜንና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለሚገኙ የተመረጡ 9 የመሰናዶ ት/ት ቤት ተማሪዎች በተመሳሳይ ቦታው ድረስ በመሄድ ትምህርቱን እንደሚሰጡ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር በውቀቱ ገልጸዋል፡፡



