በታላቁ ህድሴ ግድብ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ
ውይይቱን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት ክቡር አቶ ደመቀ መኮነን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር “ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ዲፕሎማት ነው በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎቻችን በዚህ ዘርፍ በምርምር የዳበረ ሀሳብን በመያዝ ተማሪዎቻችን ቀጣይ ሀገር ተረካቢዎች እንደመሆናቸው መጠን እነርሱም ጉዳዩን በባለቤትነት እንዲይዙት በማድረግ ስራ የምንሰራበት እና በአባይ ጉዳይ ህዝቡን አንቀሳቅሰን ሀገራችን እንዳትለማ የሚገዳደሩ ሀይሎችን ልንቋቋም ይገባል” ብለዋል
እንደ አቶ ደመቀ መኮነን አባባል “ሀገራችን በራሷ ውሃ፤ በራሷ ምድር፤ በራሷ ሀብት ለምትገነባው ግድብ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ዓለምአቀፍ ጫና በሀገራችን ላይ ለማሳረፍ እና ወደ ከፍታው የምናደርገውን ጉዞ ለማደናቀፍ ግብፅና ሱዳን ከመቸውም ጊዜ በላይ እየተረባረቡ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተማሪዎችና ተመራማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያው ዘርፍ ከፍተኛ ትግል ልናደርግ ይገባል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት ክቡር ዶ/ር ስለሽ በቀለ የውሃና መስኖ ሚኒስቴር ሚኒስትር በበኩላቸው “ሀገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያለባት፣ ህዝቧ በከፍተኛ የድህነት ውስጥ የሚኖር እንዲሁም እንደ ሀገር ዝቅተኛ የመሰረታዊ ፍጆታዎች ያሉንና ይህንን ለማሸነፍና ከድህነት ለመውጣት ቀን ከሌት እየሰራን ቢሆንም ሌሎች ሀገራት ግን ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍልን አንፈልግም በማለት ለልማታችን ተቃዋሚ ሁነው ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ሁላችንም በርትተን ልንሰራ ይገባል፡፡ የግድባችን የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ሙሉ በሙሉ የተዘጋጁ ሲሆን የግንባታ መጠናችንም በአሁኑ ወቅት 80.2% ላይ ያለ በመሆኑ ሁለተኛው የውሃ ሙሊትና ሌሎች ተግባራት በተያዘላቸው ጊዜ ይከናወናሉ” ብለዋል
በዕለቱ በመምህር ይግረማቸው እሸቱ የተሰራ እና በዩኒቨርሲቲዎች ለሚቋቋመው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላት ማሳለጫ የሚሆነው “የአባይ ልጆች” ሶፍትዌር ገለፃ ተደርጎበት ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
በበይነ-መረብ ውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን፣ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ፣ የውኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሽ በቀለን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲም የዩኒቨርሲቲ ካውንስል አባላት፣ መምህራንና የተማሪዎች ሕብረት ተሳትፈዋል፡፡

የበይነ-መረብ ውይይቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ጋር በመተባበር አዘገጅቶታል፡፡



