በትምህርት ቤት ማሻሻያ እቅድ አዘገጃጀት ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት እና በጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የጋራ ትብብር በየዳ እና ጠገዴ ወረዳዎች ለሚገኙ ርዕሳነ መምህራን, ሱፐርቫይዘሮች እና የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ባለሙያወች ስልጠና ተሰጠ፡፡ ስልጠናው ለተማሪዎች መማር እና የመማር ውጤት መሻሻል ትልቅ ሚና ባለው በትምህርት ቤት ማሻሻያ እቅድ አዘገጃጀት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ከሰኔ20 — 21/2010 ዓ.ም በደባርቅ ከተማ ካፍቴሪያ አዳራሽ ተሰጥቷል፡፡
[widgetkit id=9222]
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ፣ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን፣ በትምህርት ቤቶች የሚታዩ የግብዓት ችግሮች እንዲሁም ምቹና ጤናማ የትምህርት አካባቢ አለመኖር ለትምህርት ጥራት አለመረጋገጥ ከፍተኛ ተፅኖ አንዳላቸው ገልጸዋል ስልጠናውን በንግግር ሲከፍቱ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር ለመምህራን እና ለትምህርት ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች በመስጠት እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን በቁሳቁስ በመደገፍ የበኩሉን እየሰራ እንደሚገኝ አክለው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በየወረዳዎች በመንቀሳቀስ በትምህርት፣ በጤናው እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ በርካታ ስራዎችን እንደሚሰራም በመጨረሻ ገልፀዋል፡፡
ስልጠናው የተቋማቱን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር ተደግፎ በሙያው ሰፊ ልምድ ባላቸው የጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህራን በአቶ የሻምበል ፀሀዩ እና በአቶ ግርማ ዳኛው በትብብር ተሰጥቷል፡፡ ሁሉም ስራ መሰራት ያለበት በእቅድ መሆኑን እና እቅዱም ጥራት ካለው ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል በስልጠናው ተገልጿል፡፡ የትምህርት ቤት ማሻሻያ እቅድ የማያቋርጥ እና ኡደታዊ መሆን አለበት የሚል ሀሳብ ተነስቷል፡፡ ለዚህም የትምህርት ቤት አመራሩን እና አሰራሩን ለማሻሻል ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡
ተመሳሳይ ስልጠና ከዚህ ቀደም በምስራቅ በለሳ ወረዳ ለሚገኙ 80 ያህል ርዕሰ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች መሰጠቱን እና ወደፊት በሻሁራ እና ቋራ ወረዳዎች ለሚገኙ ርዕሰ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች እንደሚሰጥ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታው ገልጸዋል፡፡ ስልጠናው በዚህ ወቅት መሰጠቱ ለቀጣይ (2011)የትምህርት ዘመን ለሚዘጋጀው እቅድ በተሸለ መልኩ ለማዘጋጀት እና በጉዳዩ ያሉ ክህሎት ክፍተትን ለመሙላት ይረዳል ተብሏል በስልጠናው፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች አቶ ሙሌ ተቀባ እና አቶ ምህረት ተስፋዬ ዩኒቨርሲቲው እየሰጠ ያለውን የማህበረሰብ አገልግሎት አድንቀው፣ ዩኒቨርሲቲው ለመምህራን እና ለትምህርት ባለሙያዎች የሚሰጠው የክህሎት ስልጠና አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ትምህርት ቤቶችን በተለይ በቋንቋ እና ሳይንስ ትምህርቶች ያለባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በጥናት እና ምርምር የተደገፉ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
ህ/ዓ/አ/ግ/ዳይሬክቶሬት



