በነጥብ ድልድል ስርአት መሰረት በሀይሌ ሪዞርት አዳራሽ ውይይት አድርገዋል
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን በነጥብ ድልድል ስርአት መሰረት ከደረጃ 9 እስከ 18 የተመደቡ ሰራተኞች ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር የካቲት 14/2012ዓ/ም በሀይሌ ሪዞርት አዳራሽ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይት መርሀ ግብሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጋሻው አንዳርጌ፣ የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አስማማው ተገኝተዋል፡፡

ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ሀሳብ በዶ/ር አስራት አፀደወይን ቀርቧል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረው፣ የሚያከናቸው የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የመማር ማስተማርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎቹን በማጎልበት አለማቀፋዊ ዩኒቨርሲቲ እየሆነ የመጣበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ተጠቃሚ ለማድረግ የሰራቸውን በርካታ ስራዎች እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አርአያ ሊሆን የሚችልበትን እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ሊያመጣ ስለሚችለው የጎንደፈር ቤተሰብ ፕሮጀክትም አንስተዋል፡፡

በስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን የነጥብ ድልድል ዙሪያም ዩኒቨርሲቲው ካለው በርካታ የሰራተኛ ቁጥር የተነሳ በፍጠትነት አጠናቆ ወደ ስራ ለመግባት ትንሽ ቢዘገይም ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እና ተቋማት ተሞክሮዎችን ወስዶ ብዙ ክፍተቶች ሳይፈጠሩ ወደ ስራ ተገብቶ ድልድሉ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡

ይሁን እንጅ ከድልድሉ ጋር ተያይዞ በዩኒቨርሲቲው የስራ ባህል መቀዛቀዝ እየታየበት ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ፊት የስራ ስምሪቱ እና ከአንድ የስራ ክፍል ወደ ሌላው የስራ ክፍል የሚደረገው ሽግግር ምን መምሰል አለበት በሚል በሰራተኞች እና በከፍተኛ አመራሩ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ተወያዮችም በበኩላቸው በድልድሉ ዙሪያ የታዩ ክፍተቶችን አንስተዋል፡፡ በተለይ ደረጃቸው ዝቅ ብለው የመጡ የስራ መደቦች እንደገና መጠናት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
ያልተጠኑ የስራ መደቦች እንዲጠኑ እንዲሁም ያልተካተቱ የትምህርት ዝግጅቶች እንዲጠኑ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት መደረግ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ በተለይ አሁን ለተፈጠሩ አንዳንድ ቅሬታዎች መነሻ እንደክፍተት የሚወሰደው የስራ አፈፃፀም የውጤት አሰጣጥ ወጥነት የሌለው በመሆኑ ነው ሲሉ አንስተዋል፡፡ በመሆኑም ወደፊት ሰራተኞች በስራቸው ልክ መመዘን እንደሚገባቸው ተነስቷል፡፡
በመጨረሻም በሰራተኞች ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡



