በአዮዲን የበለፀገን ጨው አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማህበረሰብ አገልግሎት ለዳባት ወረዳ ለ27ቱ ቀበሌ ለሴቶች የልማት ቡድን መሪዎች በአዮዲን የበለፀገ ጨው አጠቃቀምን ለማሻሻል የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከየካቲት 17-18/2012ዓ/ም በዳባት ከተማ ሰጠ፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አይሸሽም ካሳሁን በመክፈቻ ንግግራቸው ስልጠናው በቤተሰብ ደረጃ በአዮዲን የበለፀገ ጨው አጠቃቀምን ላይ የተሳሳቱ አመለካከቶችን፣ እምነቶችን እና የእውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት ታስቦ ለሴቶች የልማት ቡድን መሪዎች መሰጠቱ ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል፡፡

በፕሮጀክቱ አባል በሆኑት የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋም መምህራን ስልጠናው የተሰጠ ሲሆን፣ የአዮዲን ምንነት እና በአዮዲን እጥረት የሚመጡ የጤና ችግሮች፣ ለአዮዲን እጥረት ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የአዮዲን እጥረት መንስኤዎች፣ ማህበረሰቡ ስለ አዮዲን እጥረት ያለው ግንዛቤ፣ የአዮዲን እጥረት መከላከያና መቆጣጠሪያ ዘዴዎች እና በሌሎች ተያያዥ ርዕሶች ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ ከየካቲት 19-20/2012ዓ/ም ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ ለጤና ባለሙያዎች እና በአዮዲን የበለፀገ ጨው ነጋዴዎች ስልጠናው እንደሚሰጥ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አይሸሽም ገልፀዋል፡፡



