በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን በተመለከተ የባለድርሻ አካላትን አቅምና የማህበረሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ በአለፋ እና በጣቁሳ ወረዳዎች ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት የካቲት 22 እና 23/2013ዓ/ም በደልጊ ከተማ የአስተዳደር የስብሰባ አዳረሽ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ከየወረዳዎቹ የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የእድር አመራሮች፣ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከፍትህ፣ከሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቡድን መሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

ፕሮግራሙን የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር መስፍን ደስዬ በንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ በንግግራቸውም ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለያዩ የስልጠና ርእሶች ዙሪያ ስልጠና ሲሰጥ እንደቆየ አውስተዋል፡፡ ዶ/ር ሰለሞን አያይዘው በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዙሪያ የሚሰጠው ስልጠና በዋነኝነት የባለድርሻ አካላትንና የማህበረሰቡን አቅም መገንባትና ተሳትፎን ማሳደግ ላይ እንደሚያተኩር ገልፀው ሰልጣኞች አፅንዖት ሰጥተው እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡
ይህ ስልጠና ባለድርሻ አካላትና የማህበረሰብ ክፍሎች ስለ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ፅንሰ ሃሳብና ጠቀሜታ ግንዛቤ በማስጨበጥ በየአካባቢያቸው የሚገኘውን ህብረተሰብ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ያለውን ፋይዳ የማስገንዘብ፣ የሚከሰቱ ኩነቶችን የማስመዝገብና የምስክር ወረቀት የማግኘት ሚናቸውን እንዲወጡ በማስቻል የምዝገባውን ጥራትና ሽፋን በማሳደግ ለህጋዊ፣ ለአስተዳደራዊና ለስታስቲክሳዊ የመረጃ ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግን አላማ ያደረገ እንደሆነ በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የስነ-ህዝብ ትምህርት ክፍል መምህርና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ የሆኑት መምህር ብስራት ወርቁ ገልፀዋል፡፡

ስልጠናው በስነ-ህዝብ ትምህርት ክፍል መምህራን በመምህር ብስራት ወርቁ፣ በመምህር አማረ ታዘበና በመምህር ንጉሴ አህመዲን አማካኝነት በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ፅንሰ-ሀሳብና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አፈፃፀም ዙሪያ ገለፃ ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም በህግ ትምህርት ቤት መምህር በሆነችው በመምህር ፈዲላ ሼሔቦ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ህጋዊ ማዕቀፍ ላይ ገለፃ የተሰጠ ሲሆን፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ቡድን መሪ በሆኑት በአቶ ወጣ ባዜ በቀጣይ ጊዚያት ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚከናወኑ ተግባራትን መለየት በሚል ርዕስ ገለፃ ተሰጥቷል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይህንን ስልጠና ቁልፍ ለሆኑ ባለድርሻ አካላት መስጠቱ ሚናቸው ምን እንደሆነ ግንዛቤ የሚፈጠርና የተሻለ አፈፃም እንዲኖር የሚረዳ መሆኑንና ይህ ደግሞ ማህበራዊና ሀገራዊ ፋይዳው ከፍ ያለ እንደሆነ ያላቸውን እምነት የገለፁት ያነጋገርናቸው የስልጠናው ተሳታፊና የአለፋ ወረዳ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቡድን መሪ አቶ ንጉሱ ምስጋናው ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡



