በደንቢያ ወረዳ የወተት እሴት ሰንሰለትን ማሻሻል በሚል ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ በደንቢያ ወረዳ ለሚገኙ የወተት አምራች ገበሬዎች፣ነጋዴዎችና የህብረት ስራ ማህበራት ሰራተኞች የወተት እሴት ሰንሰለት ማሻሻልን በተመለከተ በ01/04/2013 ዓ.ም. በቆላድባ ከተማ የአንድ ቀን ስልጠና ሰጥቷል ፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር ህትመት አስተባባሪ የሆኑት አቶ በየነ ደርሶ የስልጠናውን ጥሪ አክብረው ለተገኙ ሰልጣኞች ምስጋናቸውን አቅርበው፣ የወተት እሴት ሰንሰለት ማሻሻል ስልጠናው የወተት ልማት እድገት ለማምጣት እጅግ በጣም ጠቃሚ በመሆኑ ተሳታፊዎች በተገቢው ሁኔታ እንዲከታተሉ በማሳሰብ መርሀ-ግብሩን አስጀምረዋል ፡፡
ስልጠናውን ከሰጡት መካከል በግብርና ምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርት የሆኑት ወይዘሪት ቤተልሄም ፀዳሉ እንደገለፁት ስልጠናው የወተት እሴት ሰንሰለት ለማሻሻል ፤አርሶ አደሩ ምርቱን በዘመናዊ መልኩ ማዘጋጀት እንዲችል እና ተጠቃሚነቱ ከፍ እንዲል፤የህብረት ስራ ማህበራትም ጀምረውት የተቋረጠውን የወተት ልማት ስራቸውን ለማበረታታትና ለመስጀመር ከፍተኛ ጥቅም አለው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የስልጠናው ተካፋይ የነበሩት የገበያ ደንቦስኬ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጉልትነሽ ፈለቀ ስልጠናው እንዴት የወተት ላሞችን ንፅህና መጠበቅ እናዳለብንና የወተት ምርትን መጨመር እንደሚቻል ትምህርት ሰጥቶናል በማለት የተናገሩ ሲሆን የሳልጅገበባ ጭሎ ነዋሪ የሆኑት ቄስ ወንዳለ መላክአለው በበኩላቸው ስልጠናው ጀምረን ያቋረጥነውን የህብረት ስራ ማህበር ተግባራችን እንደገና እንድንሰራው እገዛ ያደረገልን ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይህን ለእኛ አስቦ በማምጣቱ ተደስተናል ስሉ አስረድተዋል፡፡
ስልጠናው በተለያዩ ርዕሶች እና አሰልጣኞች የተሰጠ ሲሆን ቁጥራው ከ55 በላይ የሆኑ ሰልጣኞችም ተገኝተውበታል፡፡
****************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ታህሳስ 2/2013 ዓ.ም







