በጎርጎራ የተቀናጀ የአትክልትና ፍራፍሬ ሰርቶ ማሳያ የተሰሩ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ለተለያዩ አጋር አካላት ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ በምዕራብ ደምቢያ ወረዳ በጎርጎራ የተቀናጀ የአትክልትና ፍራፍሬ ሰርቶ ማሳያ የተሰሩ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን በአርሶ አደሮች የመስክ ቀን ሚያዚያ 16/2013ዓ/ም ለተለያዩ አጋር አካላት አስተዋውቋል፡፡

በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጨቅሉ፣ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ከሃሊ ጀምበሬ፣ የኮሌጁ መምህራን፣ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ፣ ከሴቶችና ህፃናት፣ ከምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ግብርና፣ የልማት ጣቢያ ሰራተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለሙያዎችና አጋር አካለት ተገኝተዋል፡፡
የጎርጎራ ሰርቶ ማሳያ ጣቢያ ለበርካታ አመታት በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ጣቢያ እንደሆነና በተለይም በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ ቴክኖሎጂዎችን አባዝቶ በመስጠት መጠነ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ከሃሊ ጀምበሬ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው በስፋት አብራርተዋል፡፡ ጣቢያው ለተማሪዎች የተግባር ስልጠና የሚሰጥበትና ለምርምር ስራዎቻቸው የሚገለገሉበት እንደሆነ ዶ/ር ከሃሊ አክለው ገልፀዋል፡፡

የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጨቅሉ በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግራቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ለፋብሪካዎችና በአካባቢው ለሚያለሙ ባለሀብቶች ግብአት የሚሆኑ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ብቁ የሆኑ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እንዲያመርቱ ትልቅ የሰርቶ ማሳያ ቦታ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ ወደፊትም ዩኒቨርሲቲው አሁን እያደረገው ካለው ድጋፍ በበለጠ በመደገፍ የእርሻ ጣቢያውን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ብዙ ስራዎችን እንደሚሰራ ዶ/ር ቢኒያም አያይዘው ተናግረዋል፡፡

በመቀጠል በኮሌጁ የሆርቲካልቸር መምህርና ተመራማሪ በመ/ር አስራት አያሌው እና በሌሎች መምህራን በጎርጎራ የተቀናጀ አትክልትና ፍራፍሬ ሰርቶ ማሳያ ስለተመረቱ አትክልትና ፍራፍሬዎች ማለትም የተዳቀሉ የሀብሀብ፣ የቀይ ሽንኩርት፣ የቲማቲም፣ የሙዝ፣ የማንጎ፣ የብርቱካንና የሌሎችን አትክልቶች ምርታማነትና ሌሎች ባህሪያቶቻቸው ዙሪያ ሰፊ ገለፃ ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም በአብርጅሀ ቀበሌ በመገኘት ከገጠር ሴቶች የራስ አገዝ ቡድንን በመጎብኘት በቡድኑ የስራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዕለቱ ሰርቶ ማሳያው ላይ የቀረበውን ገለፃም መነሻ በማድረግ አስተያየቶችና ጥያቄዎች እንዲሁም ወደፊት ትኩረት የሚሹ ነጥቦች በዝርዝር ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶ መርሃ-ግብሩ ተጠናቋል፡፡




