በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አይሲቲ ዳይሬክቶሬት የለሙ ሶፍትዌሮች ትውውቅ ተደረገ !!
የትውውቅ መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት ዶ/ር አስራት አፀደወይን እንደገለፁት “ ዩኒቨርሲቲያችን በቀዳሚነት ስሙ እንዲጠራ ካስቻሉት በዋናነት የሚጠቀሰው የአይሲቲ መሰረተ ልማት ነው ፡፡ ዛሬ በዓለማችንና በሀገራችን ቴክኖሎጅ በፈጣን እድገት ላይ ይገኛል በመሆኑም እኛም በራሳችን ተቋማት የምናለማቸውን በመስራት ከሌሎች የምናገኛቸውንም ቴክኖሎጅ ሽግግር በመጠቀም የጀመርነውን የልማት እና የእድገት ደረጃ ማስጠበቅ ይጠበቅብናል፡፡ በዛሬው ዕለት ተሰርተውና ተጠናቅቀው ለትግበራ የቀረቡ ሶፍትዌሮች በሁሉም ተቋሞቻችን በባለቤትነት መያዝ ይገባቸዋል ተፈጻሚነታቸውንም መከታተል ይገባል” ካሉ በኋላ የሶፍትዌር ልማት ቡድኑንና ይሄን ስራ እያስተባበረ የሚገኘውን የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ቢሮን አመስግነዋል፡፡

የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሰረት ካሳ በበኩላቸው “በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአይሲቲ ዳይሬክቶሬት የሶፍትዌር ልማት ቡድን በዚህ ዓመት የተለያዩ ሲስተሞችንና ሶፍትዌሮችን በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ክፍሎች ጥያቄና በከፍተኛ አመራሩ ተገቢነታቸው ተረጋግጦ ተሰርተዋል፡፡ የአይሲቲ ዳይሬክቶሬቱ ተቋማዊ የአይሲቲ ፖሊሲ እና በርካታ የመተግበሪያ ሶፍትዌሮች መስራቱ የሚታወቅ ሲሆን የዛሬው መርሃ ግብርም ደግሞ የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ተሰርተው በቀረቡት ሶፍዌሮች ላይ ግንዛቤ እንዲያገኝና ወደ ትግበራ እንዲገባ ለማስቻል የተዘጋጀ ነው” ብለዋል፡፡

የሶፍትዋር የልማት ቡድን ከተያዩ ተቋማት በቀረቡና ታምኖባቸው የተፈቀዱ ስምንት ሶፍትዌሮችን ለማልማታ መቻሉን ከውይየቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡




