በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተከናወኑ ባሉ ወቅታዊ ተግባራት ላይ ጉብኝት ተደረገ
በኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ዶክተር ሊያ ታደሰ የተመራ የልዑካን ቡድን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየተከናወኑ ያሉ ወቅታዊ ተግባራትን ጎበኙ፡፡
በጉብኝቱ ከክብርት ዶክተር ሊያ ታደሰ በተጨማሪ የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ክብርት ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው፣ የጤና ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶር ደረጀ ድጉማ፣ በመከላከያ ሰራዊት የጤና መመሪያ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ፣ የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶር አብዱልቃድር ገልገሎ፣ የአማራ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶር መልካሙ አብቴ እና ሌሎች የልዑካን ቡድኑ አባላት የተገኙ ሲሆን፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየተከናወኑ ያሉ ወቅታዊ ተግባራትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ በሀገራችን ህግን በማስከበር ተግባራት ተሰልፈው ጉዳት የደረሰባቸውን የሰራዊት አባላት እና ከሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል በህውሃት ታፍነው ቆይተው የተለቀቁ ከ1500 በላይ የሆኑ የሰራዊት አባላትን የጎበኙ ሲሆን ከጉብኝቱ በኋላ ውይይት ተካሂዷል።
በተደረገው ውይይት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሥራት ዓፀደወይን ተደርጓል። ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ጦርነቱ ባልተጠበቀ ሰዓት የተከፈተ ቢሆንም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጦርነቱ ከተጀመረበት ማግስት ጀምሮ የሚጠበቅበትን ተቋማዊ ግዴታ ለመወጣት እቅድ አውጥቶ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን፣ የሆስፒታል አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት በዋናነት ይጠቀሳሉ ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የሕክምና ሥነ-ምግባር በጠበቀ መንገድ ከምንጊዜውም በላይ እያደረገ ነው ያሉት ኘሬዚዳንቱ በሂደቱ የተሳተፉ ሀኪሞችን፣ የጤና ባለሙያዎችን እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላትን፣ የጎንደር ከተማ በጎ ፈቃድ ወጣቶችን፣ የጎንደር ከተማ ሕዝብና አስተዳደርን፣ በአገር ውስጥና በተለያዩ አገራት ያሉ ግለሰቦችና ድርጅቶችን፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ያልተቆጠበ ወገናዊ ድጋፍ ላደረጉልን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል።
በምክትል ኘሬዚዳንት ማዕረግ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትና ያጋጠሙ ችግሮችን በዝርዝር አቅርበዋል።
በውይይቱ የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በክብርት ዶክተር ሊያ፣ ክብርት ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባውና ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ ማጠቃለያ ተሰጥቷል።
በማጠቃለያቸውም ሀገራችን ለገጠማት ችግርና መንግስት ህግን ለማስከበር እየወሰደ ባለው ተግባር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ዝግጅትና እያከናወነ ላለው የሚያኮራ ተግባር ከፍተኛ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ የጎንደር ከተማ ህዝብና ወጣቶችም ላከናወኑት መልካም ተግባር አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደማይለያቸውም አረጋግጠዋል። የሰራዊቱ አባላትም ዩኒቨርሲቲውና የጎንደር ከተማ ህዝብ ላደረገላቸው የተለየ አቀባበልና አያያዝ መደሰታቸውን በጀኔራል ጥጋቡ በኩል ገልፃዋል።
*********************************************
ሀገራችን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 27/2013 ዓ.ም






